ቀጥታ፡

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

ሚያዝያ 26/2011 የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድርግ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች አቀባባል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽና በአገራቱ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።

በነገው እለትም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ደቡብ ሱዳንና አንጎላንም እንደሚጎበኙ ከጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያና ጃፓን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1930 ሲሆን እ.አ.አ በ1958 አገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን ከፍተዋል።

ሁለቱም አገራት በልማቱ መስክ ጠንካራ ትብብር ያላቸው ሲሆን የጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ጃይካ) በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ ስራዎች የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

አገራቱ በንግዱ ዘርፍ መልካም ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ ወደ ጃፓን ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመሞችን ስትልክ መኪናዎች፣ የማሽነሪ እቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክስና የህክምና እቃዎች እንዲሁም የብረታ ብረት ምርቶችን ደግሞ ከጃፓን ታስገባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም