የቀደመ ህብረታችንንና አንድነታችንን እናጠናክራለን…የአማራና የቅማንት ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
የቀደመ ህብረታችንንና አንድነታችንን እናጠናክራለን…የአማራና የቅማንት ተወላጆች
ሚዝያ 26/2011 የአማራና የቅማንት ህዝቦች በካከላቸው የተከሰተውን ቅራኔ በመርሳት የቀደመውን አብሮነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።
ዛሬ በጎንደርና አካባቢው የሰላምና ልማት ማህበርና በአዲስ አበባ የጎንደር ተወጆች የተመሰረተው መልሶ ማቋቋም አስተባባሪ ኮሚቴ አዘጋጅነት ለሁለቱ ወገኖች ተፈናቃይ ዜጎች የምሳ ግብዣ ተደርጓል።
ከተጋባዦች መካከል አቶ ወርቁ ጌጡ እንደተናገሩት ይህ የጋራ ምሳ ግብዣ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ህዝቦች በማህበራዊ መስተጋብሮችና በጉርብትና ላይ የነበራቸውን አንድነት እንዳስታወሳቸው ተናግረዋል፡፡
በምንም መልኩ የማይለያዩ ህዝቦች በሴረኛ ፖለቲከኞች ምክንያት አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ በጋራ ተገናኝተው በመወያየት ዳግም ወደ ነበሩበት የአብሮነት ህይወት መመለስ መቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
“እንደምን ልጅና አባት፣ እናትና ልጅ እንዲሁም ባልና ሚስት ተለያይተው ይኖራሉ?” ያሉት አቶ ወርቁ በግጭቱ ምክንያት ቤታቸውና ንብረታቸው ባስ ሲልም ልጃቸውን ቢያጡም ከልባቸው ይቅር ማለታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሌላኛው ተጋባዥ ወጣት ሙሉአለም አስማማው በበኩሉ “ከዚህ በፊት አብረን ስንበላ እና ስንጠጣ የነበርን ጓደኛየን በጊዜያዊ ችግር ምክንያት በውስጤ ቂም ብይዝበትም አሁን በአንድ ስንገናኝ እምባችን መቆጣጠር አልቻልንም” ብሏል፡፡
በቀጣይም ግንኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር ለጋራ እድገት እንደሚሰሩ አረጋግጧል፡፡
ከመተማ ጊዜያዊ መጠለያ የመጡት አቶ ሰማ አንዳርጌ በአንፃሩ የምሳ ግብዣው ፍቅራቸውን ያጠናከረና ፊት ለፊት ተገናኝተው ይቅር ያባባለ በመሆኑ ለአዘጋጅ ኮሚቴዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የዚህ ምሳ ግብዣ አዘጋጅ ኮሚቴና በጎንደርና አካባቢው የሰላምና ልማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ ድርጅት አድማሴ እንዳሉት ዝግጅቱ ሁለቱ ህዝቦች የነበራቸውን አብሮ የመብላትና የመጠጣት ወግ እንዲመልሱ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡
“በሁሉም አካባቢዎች በሚደረግ እርቅም ይህ ማህበር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል” በማለት በማህበሩ አማካይነትም ከአሁን በፊት ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
በምሳ ግብዣው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕርግ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ተፈናቃዮች በዘላቂነት የማቋቋም ግብረ ኃይል የበላይሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በሁለቱ ህዝቦች በውል ባልተረዱት ምክንያት የተፈጠረውን መለያየት መልሶ ለማገናኘት እንደማይከብድ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ሁሉንም ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት ለመመለስ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ጥረት እያደረገ ሲሆን የሚመለከተው አካል ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በምሳ ግብዣው የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በሁለቱም ዞኖች ከሚገኙ 13 መጠለያ ጣቢያዎች የመጡ ከ1ሺህ 300 በላይ ተፈናቃዮች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።