ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን በተከሰተ ግጭት የንጹሐንን ህይወት ያጠፉ ለህግ ይቅረቡ…ነዋሪዎች

ሚያዝያ 26/2011 ከትላንት በስቲያ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን መዳኔ በተባለ ወረዳ በተነሳ ግጭት የንጹሐንን ህይወት ያጠፉ አካላት ለህግ ሊቀርቡ እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠየቁ

ከዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች የተወጣጡ ነዋሪዎች ዛሬ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ እንደገለጹት የክልሉ ካቢኔ ላለፉት አራት ዓመታት በአፋር ክልል ስር ሲተዳደሩ የነበሩ ሶስት የዞኑ ቀበሌዎች ወደ ክልላቸው እንዲመለሱ ያሳለፈውን ውስኔም ደግፈዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የሽንሌ ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት ሰልፍ ከትላንት በስቲያ መዳኔ በተባለ ስፍራ የንጹሃን ዜጎችን ህይወት ባጠፉት ኃይሎች ላይ የፌዴራል መንግስት ተገቢውን ቅጣት በመስጠት ዘላቂ ሰላምን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል።

በሰልፉ ላይ የተሳተፉት የዞኑ ሽማግሌ ሐጂ ሙሳ ሚጋድ ለኢዜአ እንደገለፁት በንጹሃን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ጉዳት ማስቆም አስፈላጊ ነው።

“ከትላንት በስቲያ የተፈፀመው ተመሣሣይ ግድያም ቀጪና ጠያቂ በመጥፋቱ ነው ፤የፌደራል መንግስት እነዚህን አጥፊዎች ለህግ ሊያቀርብ ይገባል”ብለዋል።

የአፋርና የሶማሌ ክልል ወንድማማች ህዝቦች ለዘመናት በፍቅርና በአንድነት የሚኖሩ መሆናቸውን አስታውሰው "ይህን ጠንካራ ግንኙነት ለመጠበቅ አዛውንቶች ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ” ብለዋል፡፡

“በአፋር ክልል ሥር የሚተዳደሩት ገርባ ኢሴ ፤ ሁንዱፎና አዴይቲ ቀበሌዎች የሚገኙ ዘመዶቻችን ላይ እየደረሱ የሚገኙ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶችን እንቃወማለን፤ ፍትህ ለወገኖቻችን” ያሉት ደግሞ ሌላው በሰልፉ የተሳተፉት አቶ ጣሂር ሙሣ ናቸው፡፡

እንደ አዛውንቱ ገለፃ ሰልፉ ሶስቱን ቀበሌዎች አዲሱ የክልሉ ካቢኔ ወደ ክልላቸው እንዲመለሱ በመወሰኑ ደስታቸውን ለመግለፅ ነው፡፡

“ወይዘሮ አይሻ ሐሰን በበኩላቸው የክልሉን ውሳኔ እንደግፋለን፤ ውሳኔውን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግና የገርባ ኢሴ፤ ሁንዱፋ፤ አዴይቲ ነዋሪዎች የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል” ብለዋል፡፡

“የፌዴራል መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባዋል” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋጡማ ፉራህ ናቸው፡፡

"በሰላም ዕጦትና በግጭት የሚጎዱት ሴቶችና ህጻናት ናቸው"በማለት በየጊዜው የሚፈጠረው ትንኮሳ፣ ግድያና ሰላምን ማደፍረስ እንደሚቃወሙት ገልጸዋል።

ሰልፉን ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል የዞኑ ወጣቶች /በርበርታ/ ሊቀመንበር ወጣት ጣሂር ፋራህ ሰመሬ መዳኔ በተባለ ሥፍራ የተፈፀመውን ግድያ ወጣቶች ማውገዛቸውን ተናግሯል፤ አጥፊዎቹ ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙም ጠይቋል፡፡

“አዲሱ የሶማሌ ክልል መንግስት ካቢኔ በአፋር ክልል ሥር ሲተዳደሩ የነበሩ ሶስቱ ቀበሌዎች ወደ ሱማሌ ክልል እንዲመለሱ መወሰኑ ወጣቶችን አስደስቷል” ብሏል፡፡

በአፋር ክልል በአዋሽና በአሳይታ የታሰሩ ሰዎች መለቀቅ እንዳለባቸው የተናገረው ወጣት ጣሂር “የዞኑ ወጣቶች ለሀገር ሰላምና ደህንነት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ” ብሏል።

ወጣቱ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርና የአካባቢውን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ተገን በማድረግ ሰላምና የሀገርን ጥቅም ለማደፍረስና ጥፋት ለመፈፀም የሚደረግን ማናቸውንም እንቅስቃሴ በንቃት እንደሚመክት ነው የገለፀው፡፡ 

በተመሣሣይ ዜና በድሬዳዋ የሚገኙ የሶማሌ ተወላጆችና ወጣቶች ዛሬ ባደረጉት ሰልፍ ላይ እንዳንፀባረቁት፤ የክልሉ ካቢኔ ትላንት በአፋር ክልል ሥር ሲተዳደሩ የነበሩ የሲቲ ዞን ቀበሌ የሆኑት ገርበ ኢሴ ፤ሁንዱፎና አዴይቲ ቀበሌዎች ወደ ክልሉ እንዲመለሱ መወሰኑ አስደስቷቸዋል፡፡

ሰልፈኞቹ ከትላንት በስቲያ በዞኑ መዳኔ በተባለ ስፍራ በተገደሉት ወገኖቻቸው የተሰማቸውን ኃዘን ገልፀው የፌዴራል መንግስት አጥፊዎችን ለህግ እንዲያቀርብና የህግ የበላይነትን እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር ጉዳዩን አስመልክቶ የአፋር ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም