ቀጥታ፡

የሁለተኛው ዙር የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች ተጀምሯል

አዲስ አበባ  ሚዝያ  26/2011  የሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል።

የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 23 ለ 22 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በጨዋታው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ያሳየው እንቅስቃሴ ካለው ወቅታዊ ብቃት አንጻር በጣም ደካማ የነበረ ቢሆንም በጨዋታው መገባዳጃ አካባቢ መነቃቃት በማሳየት ከመመራት ተነስቶ ተጋጣሚውን ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን በጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

በአንጻሩ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በጨዋታው ያገኟቸውን ግብ የማስቆጠር እድሎች በአጨራረስ ድክመት ምክንያት አለመጠቀማቸው እና የመከላከል ማነስ ለሽንፈት ዳርጓቸዋል።

ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የዛሬውን ድል ጨምሮ እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጋቸውን 10 ጨዋታዎች በማሸነፍ ስኬታማ ግስጋሴውን ቀጥሎበታል።

ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሽንፈቱን ተከትሎ በሰባት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።

የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቡታጅራ ከተማን 48 ለ 22 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ልዩነት ማሸነፍ ችሏል።

ጨዋታው የባለሜዳው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፍጹም የበላይነት የታየበት ሲሆን ተጋጣሚው ቡታጅራ ከተማ ከአቅምና ከልምድ አኳያ ከተጋጣሚው ቡድን ጋር በጣም ሰፊ የሚባል ልዩነት ነበረው።

ተመጣጣኝ ፉክከር ባልታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የተገኘው አብዛኛው ተመልካች ጨዋታው ሳይጠናቀቅ ስታዲየሙን ለቅቆ ወጥቷል።

ዛሬ በጎንደር ጎንደር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማ ወደ ስፍራው ባለማቅናቱ ምክንያት ጨዋታው ሳይካሄድ ቀርቷል።

 ድሬዳዋ ከተማ ወደ ጎንደር ያላቀናው በበጀት ችግር ምክንያት እንደሆነ መግለጹን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ተስብስቦ በጨዋታው ዙሪያ ውሳኔ እንደሚያሳልፍም ተገልጿል።

የሁለተኛው ዙር የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ሲካሄድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መከላከያ ከከምባታ ዱራሜ  ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ደቂቃ መቀሌ ላይ መቀሌ ሰብዓ እንደርታ ከፌዴራል ፖሊስ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ20 ነጥብ ሲመራ፣ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ17 መቀሌ ሰብዓ እንደርታ በ13 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ጎንደር ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።

በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 ክለቦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።  የ2011ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛው የውድድር ዓመቱ ነው።

ፕሪሚየር ሊጉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን፤ መከላከያ በ2009 ዓ.ም እንዲሁም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም