ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ኢትዮጵያን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መርቷታል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ኢትዮጵያን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መርቷታል-ምሁራን
ሚያዝያ 26/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክን በማዛባት ለፖለቲካ ፍጆታ የማዋል ዝንባሌና ተግባር ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንደወሰዳት ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የታሪክ ተመራማሪው ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ መኮንን የሰው ልጅ ያለፈው ልምድ በታሪክነት የሚያጠናው የአሁኑን ዘመን የተሻለ ለማድረግና ለወደፊቱ መሰረት ለመጣል ነው ብለዋል።
ታሪክ የሚዛባው ያለፉ ክንውኖች የመረጃ አሰባሰብ ላይ በሚከሰት ጉድለት እንደሆነም ጠቁመዋል ምሁሩ።
የታሪክ ልሂቃን መረጃ አያዛቡም ብሎ መደምደም ባይቻልም እውነታን በማስቀመጥ ረገድ ስኬታማ ናቸው ያሉት ዶክተር ተፈሪ፥ የልምድ ጸሐፊዎች ግን በባሰ ሁኔታ ታሪክን ሊያዛቡ ይችላሉ ነው ያሉት።
በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ እንዳሉት፥ የኢትዮጵያ ታሪክ የዓለም ታሪክ አካል ቢሆንም ለየት የሚደርጉት ባህርያት አሉት።
በአፍሪካ ታሪክ ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች ጥንታዊ ስነ መንግስት፣ የዳበረ ባህልና የፅሁፍ ቋንቋ ባለቤት በመሆኗ የቆዩ የታሪክ ሰነዶች ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ ስደራ በአራት ጎራ እንደሚከፈል ያነሱት ዶክተር አልማው፥ የመጀመሪያው በአሳሾች፣ በተጓዦችና ሚሺነሪዎች ሌላኛው በነገሥታት ገድል ጸሃፊዎች እንዲሁም በልማዳዊ የታሪክ ፀሃፊዎችና በታሪክ ተመራማሪዎች መጻፉን ገልጸዋል።
ታሪኮቹም የፖለቲካ ሁነት ላይ ብቻ በማተኮር የህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መስተጋብር አለማካተታቸው የድክመታቸው መነሻ እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህም የሚያግባባ አንድ የታሪክ ሰነድ እንዳይኖር ከማድረጉም ባሻገር ዘውገኛ ፖለቲከኞች ታሪክን እንደፈለጉት አዛብተው በማቅረብ ህዝብን ወዳልተፈለገ ሁኔታ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክን አዛብቶ ለፖለቲካ ፍጆታ የማዋል ዝንባሌዎች መኖራቸውን አንስተው፥ ይህም ታሪክ ከማንነት ጋር መቆራኘቱ ህብረተሰቡን በቀላል ለማነሳሳት በማስቻሉ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ ከጥንት እስከ ዘመናዊው ሲፈተሽ የነገስታቱ ገድልና የውሎ ዘገባ ፖለቲካዊ ታሪክ ላይ ማተኮሩን በድክመት በማንሳት በህዝቦች ታሪክ ላይ ትኩረት አለመደረጉ ብዙ ፈተና እንዳመጣ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ብዙ ውዝግብ መኖሩን የጠቀሱት በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ምምህሩ ዶክተር አልማው፥ በርካታ ሰዎች በኢትዮጵያ ታሪክና በጸሃፊዎች ዙሪያ እንደማይስማሙ ገልጸዋል።
በተለይ የዘውግ ፖለቲካ መቀንቀን ከጀመረ ወዲህ በታሪክ የተዳሰሰው የሰሜኑ እንጂ የኛ አልተካተተም የተጠናው የቅርብ ጊዜው ብቻ ነው የሚሉ አስተያየቶች እንደበረከቱም ተናግረዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ በአሳሾች ተጓዦችና ሚሺነሪዎች የተጻፈ በመሆኑ ዛሬ ተሰድበናል እንዲህ ተብለናል የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ይገልጻሉ።
የገድል ጸሃፊዎችም ንጉሱ ቀጥሮና ቤት ሰጥቷቸው ስለሚጽፉ፥ ስለ ንጉሱ ጉድለቶች አንድም መስመር አልጻፉም ብለዋል።
ይህም ለሀገራችን የታሪክ መዛባት ቢያስከትልም “ትናንትን መቀየር አይቻልም” ያሉት ዶክተር አልማው፥ “ከትናንት ጠንካራ ጎንን ይዞ ደካማውን ቀርፎ መጓዝ” እንዳለበት መክረዋል።
የኢትዮጵያ የምርምርና ጥናት ተቋም ላለፉት 60 ዓመታት ስለደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ስለመንግስታትና ባህል ታሪክ በርካታ ፅሁፎችን ማዘጋጀቱን የገለጹት የተቋሙ ባልደረባ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ ናቸው።
ሆኖም መንግስት ለታሪክ ያለው ዕይታ በመዛባቱ በምርምር ተቋሙ ያሉት በርካታ ምርምሮች ከሼልፍ ወርደው የህዝብን እውነተኛ ታሪክ ለማጉላት ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን ገልጸዋል።
ዶክተር አልማው በበኩላቸው በ1950ዎቹና 60ዎቹ ከአውሮፓ ተምረው በመጡ ልሂቃን የተጻፉ መጻህፍት አንዱን ብሔር ከአንዱ አንድን ሃይማኖት ከሌላው የሚያቃርኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሰሩትን አኩሪ ታሪክ ለትውልዱ በአግባቡ ማሳወቅና ማስተማር ባለመቻሉ ሀገሪቱ ወደ ኋላ እንደተጎተተች ነው ሀሳባቸውን የገለጹት።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ እንደሚሉት ፖለቲከኞች ያለፉ ነገስታትና መሪዎች የሰሩትንም ያልሰሩትንም በማጋነን ለህብረተሰቡ በማቅረባቸው የታሪክን ዓላማ አዛብተዋል።
ዶክተር አልማው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ ሁልጊዜ በመንግስትና በፖለቲከኞች ለስርቆት፣ ለንጥቂያ፣ ለውጊያ፣ ለጠለፋ መዳረጉን ነው ያስረዱት።
“ልሂቃኑ በመንደራቸው ንጉስ ለመሆን እንጅ የሚጥሩት ክፍተቱን አሟልቶ የተሻለ ለማድረግ አይደለም። አንዳንዶች አውሮፓ ድረስ ሂደው ተምረው ሲመጡ በእውቀት ከማገልገል ይልቅ የተማሩትን ለእኩይ አላማ ሲያውሉት ይስተዋላል” ብለዋል።
የታሪክ ባለሙያዎች ከሰፈራቸው ወጥተው ስለ ሀገር በመወያየትና በመከራከር ለህዝብ የሚጠቅሙ እሳቤዎችን ማውረስ ይገባቸዋል ያሉት ዶክተር አልማው፥ ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ያዋሉበትን ኪሳራ መልሰው ማካካስ እንዳለባቸውም መክረዋል።
መንግስት ለታሪክ ምርምር ተገቢውን በጀት በመመደብ፣ ለሙያተኞች ነጻ ምህዳር የመፍጠር ግዴታ አለበት ያሉት ደግሞ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተፈሪ ናቸው
አንዳንድ ልሂቃን የምርምር ሰነድ ሲያዘጋጁ ሳይንሳዊና ትክክለኛ አድርገው ሲጽፉ ቢስተዋልም፣ እነዚያው ሰዎች በጋዜጣና በመፅሄት የተዛባ የታሪክ መረጃ ሲያስተላልፉ ማየት አሳፋሪ ተግባር ነው ብለዋል።
“የህዝቦች ታረክም በአግባቡ ተሰንዶ ወደ ትምህርት መቅረቡ ለብሔራዊ መግባባት ትልቅ ፋይዳ አለው” ነው ያሉት።
ይህን የሚያስረዱ በርካታ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ የሁለተኛ ዲግሪና የሶስተኛ ዲግሪ ሟሟያ ጥናቶች ቢኖሩም ወደ አንድ የኢትዮጵያ የታሪክ ሰነድነት ባለመለወጣቸው የተፈለገውን ውጤት አላስገኙም ብለዋል።
አክለውም ምሁራኑና ፖለቲከኞች ያለፉትን የታሪክ ጉዳዮች እያዛቡ ህዝብን ከማራራቅ በጠላትነት እንዲተያይ በማድረግ ጊዜያዊ ጥቅም ከመፈለግ ሊቆጠቡ ይገባል ነው ያሉት።
“ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገሩን ታሪክ የማያውቅ ትውልድ ተፈጥሯል፤ ይህ እንድ ሀገር ክሽፈት ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች እርስ በእርስ ሲጫረሱ የኖሩ የሚመስለው በርካታ ዜጋ አለ፤ እውነታው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ተጋብቶ የተዋለደ በአንድነት የተጋመደ ነው።”
በተዛቡ መረጃዎች የሚሞላ ጭንቅላት ለሀገሪቱ አውዳሚ ቦምብ ነው፤ ቦምቡን ለማምከን የህዝቡን መስተጋብር የሚያሳየውን እውነተኛ ታሪክ ለትውልዱ ማሳወቅ ይገባል ብለዋል።