ቀጥታ፡

በአምስት ሺህ ሜትር የዳይመንድ ሊግ የሩጫ ውድድር መቅረትን ተከትሎ የተነሳው ቅሬታ አግባብነት የለውም ተባለ

አዲስ አበባ ሚያዝ 25/2011 በአምስት ሺህ ሜትር የዳይመንድ ሊግ የሩጫ ውድድር መቅረትን ተከትሎ በኢትዮጵያ በኩል የተነሳው ቅሬታ አግባብነት የለውም ሲሉ ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ ገለጹ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል የ10 እና አምስት ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድሮች በአዘጋጆቹ በኩል ፍላጎት ማነስ እየተየባቸው ይገኛል።

በቅርቡም የዳይመንድ ሊግ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውድድር ሲካሄድባቸው ከነበሩት ርቀቶች መካከል አንዱ የነበረውን የ5 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር ቀንሷል።

ይህን ተከትሎም በዚህ ርቀት ላይ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ስምና ዝና ያላቸው አትሌቶች መፍለቂያ የሆኑት የኬኒያና የኢትዮጵያ አትሌቶች በመሆናቸው የሁለቱ አገራት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ቅሬታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።


በኢትዮጵያ በኩል ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ኮሚቴ በማቋቋም ውሳኔው እንደገና እንዲታየ ለማድረግ እንደሚሰራ መግለጹ ይታወቃል።


የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና በሌሎች የተለያዩ የስፖርት ኃላፊነት ቦታዎች የሰሩት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በዳይመንድ ሊጉ የአምስት ሺህ ሜትር መቀነስን ተከትሎ በኢትዮጵያ በኩል የተነሳው ቅሬታ አግባብነት የለውም ሲሉ ነው የገለጹት።

በተለያዩ አገራት የሚደረጉ የግል የአትሌቲክስ ውድድሮች አዘጋጆቹ ሩጫውን በፈለጉት ርቀት ማካሄድ ውድድሩን የሚያዘጋጀው ድርጅት ወይም ኩባንያ መብት እንጂ የተጋባዥ አገሮች አይደለም።

በተለይ የአምስት እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ በብዛት የኬኒያና የኢትዮጵያ አትሌቶች አሸናፊ የሚሆኑበትና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የበላይነት የሚጠናቀቅ በመሆኑ ለአገራቱ ምቾት የሚሰጥ እንዳልሆነ ነው የገለጹት።


የአውሮፓም ሆነ ሌሎች አገራት ውድድሮች ሲያዘጋጁ በውድድሩ የአገራቸው ዜጎች እንዲያሸንፉ ነው ፍላጎታቸው።

ነገር ግን በብዛት በእነዚህ ርቀቶች ላይ ከፊት ሆነው ውድድሩን የሚመሩትና በበላይነት የሚያጠናቅቁት የኢትዮጵየና የኬኒያ አትሌቶች ናቸው።

ይህም የውድድሩ አዘጋጆችን አገራት ዜጎችና ሩጫውን በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ የአውሮፓ አገራትና ድርጅቶችን ደስ የሚያሰኝ አይደለም።

በመሆኑም የ10 እና የአምስት ሺህ ሜትር ርቀቶች ላይ የሚደረጉ ውድድሮች እየቀነሱ እንዲመጡ ምክንያት መሆኑን ነው ያነሱት።

ከዚህ በተጨማሪ የ10 እና አምስት ሺህ ሜትር ውድድሮች ከአጫጭርና መካከለኛ ርቀቶች በላይ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸው ለተመልካች መሰላቸትን የሚፈጥሩ መሆኑም ሌላው በምክያትነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህን ችግር ለመፍታት ቅሬታን ከማቅረብ ይልቅ የተሻለ አማራጭ የሚሆነው የቅርብ ወዳጅነት በመፍጠር መነጋገር ነው ይላሉ።

እንዲሁም አፍሪካዊያን አሁን ከሚያዘጋጁት በላይ የራሳቸውን የአትሌቲክስ ውድድሮች ማብዛት ይገባቸዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቶች  እየተሻሻለ የመጣው የ1 ሺህ 500 ሜትርና ሶስት ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ በደንብ ከተሰራ አቅም ያላቸው አትሌቶች በመኖራቸው ገፍተው መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በአንዳንድ የስፖርቱ ቤተሰቦች ዘንድ እንደ 10 እና አምስት ሺህ ሜትር ውድድሮች ሁሉ የማራቶን ውድድርም ስጋት እንዳላቸው የሚናገሩ ያሉ ሲሆን እንደ አቶ ፍቅሩ ገለጻ ግን ማራቶን ከኦሎምፒክ ታሪክ ጋር ልዩ ትስስር ስላለው የሚያሰጋ ነገር እንደሌለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም