የሁለተኛ ዙር የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ነገ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የሁለተኛ ዙር የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ነገ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ነገ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስቴዲየም ነገ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከቡታጅራ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ጎንደር ከተማ በሜዳው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ይጫወታል።
ከነገ በስቲያ እሁድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስቴዲየም መከላከያ ከከምባታ ዱራሜ ከቀኑ 9 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከፌዴራል ፖሊስ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ይጫወታሉ፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ18 ነጥብ ሲመራ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ15 ነጥብ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ13 ነጥብ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል፡፡
ጎንደር ከተማ ያለምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል፡፡
በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 ክለቦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል የ2011 ዓ.ም የሐበሻ ወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ፡፡
ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስቴዲየም አዲስ አበባ ፖሊስ ከወላይታ ድቻ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ከነገ በስቲያ እሁድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስቴዲየም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከጣና ባህርዳር ከረፋዱ 4 ሰዓት መከላከያ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ይጫወታሉ፡፡
ሮቤ ላይ ከጠዋቱ 3 ሰዓት መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከሙገር ሲሚንቶ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል፡፡
በ2011 ዓ.ም የሐበሻ ወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 8 ክለቦች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡