ኢትዮጵያ የግብር ገቢዋን ለማሳደግ የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድርግ እንዳለባት አንድ ጥናት አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የግብር ገቢዋን ለማሳደግ የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድርግ እንዳለባት አንድ ጥናት አመለከተ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2011 የአፍሪካ ልማት ባንክ ባደረገው ጥናት ኢትዮጵያ ከግብር ከፋዮች የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ የአሰራር ማሻሻያዎችን እንድታደርግ አመላከተ።
ባንኩ በጥናቱ ኢትዮጵያ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ገቢራዊ በማድረግ ገቢዋን ለማሳደግ መስራት እንዳለባትም አመላክቷል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ በፍቃደኝነት ግብር የሚከፍሉ ዜጎች ያሉበትን ደረጃ የሚያስቃኝ ጥናት አቅርቦ በአዲስ አበባ ውይይት ተደርጎበታል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የዘርፉ ባለሙያዎችና የዩንቭርስቲ ምሁራን፣ የልማት አጋሮች ፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የመንግሥት ባለስልጣናት ተሳትፈዋል።
ከአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ በግብር አሰባሰብ ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ጠቅሶ የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዳለባት አመላክቷል።
በባንኩ የጥናት ክፍል ኃላፊ አቶ አበባ ሽመልስ በውይይት መነሻ ጸሁፋቸው፤ ኢትዮጵያ ከደረሰችበት ኢኮኖሚ አንጻር ከገቢ 30 በመቶ ኢቨስትመንት ላይ ማዋል ይጠበቅባታል።
''ይሁን እንጂ እየተሰበሰቡ ያለው ገቢ ዝቅተኛ በመሆኑ ይህን ማድረግ አልተቻለችም'' ያሉት ኃላፊው አሁን ላይ 12 በመቶ ብቻ ገቢ መሰብሰቧን በምክነያትነት ይጠቅሳሉ።
"ይህም የሕዝቡን አመኔታ መመለስ እንደሚያሻ አመላካች ነው፤ ሰው እየተገደደ ግብር አይከፍልም" ብለዋል።
የሚሰበሰበው ገንዘብ ምን ላይ እየዋለ ነው ፣ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን በማረጋገጥ ኀብረተሰቡን አመኔታ እንዲያዳብር መንቀሳቀስ ይገባል ነው ያሉት።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በኢትዮጵያ 150 ሺህ ግብር ከፋይ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን ለእነዚህ ድርጅቶች መረጃን በዘመናዊ መልኩ በማቅረብ የግብር አከፋፈሉን ማቀላጠፍም ወሳኝ ነው።
"ሁሉም ታክስ ከፋይ በመንግስት እኩል መታየት አለበት" ያሉት አቶ አበበ ፍትሃዊ አሰራር በመዘርጋት የገቢ አሰባሰቡን ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የህዝቡን ግንዛቤ ለማጎልበት የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
'ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ' በሚል መሪ ሃሳብ የግብር ንቅናቄ ከመርሃ ግብሩ መካከል አንዱ መሆንኑ ጠቅሰው ከግንዛቤ ከመፍጠር ጎን ለጎን እርምጃ እየተወሰደ ነውም ብለዋል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ የተካሄደው ጥናት ዘመናዊ ቴክሎጂን መጠቀም ላይ አገሪቷ ወደ ኋላ መቅረቷን የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት ይሰራበታል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አገሪቷ ያላትን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የግብር አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ ግድ ይላል።
ይህን ለማድረግም መንግሥት የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራና የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ጠቁመው ግብረ ኃይሉ የአገሪቷን የቫት ህግና የኤክሳይስ ታክስን የመሳሰሉ ህጎችን ማሻሻል ትኩት ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በዝርዝር በመለየት የፖሊሲ ለውጥ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።