ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ስርዓተ ቀብር እሁድ እንደሚፈጸም ገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን የቀብር ስነ ስርዓት እና ብሔራዊ የሀዘን ቀንን አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ  የቀብር ስነ ስርዓቱ ሙሉ ወጪ በመንግስት ይሸፈናል፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር  ነጋሶ ጊዳዳን ድንገተኛ ሞት ተከትሎ ብሄራዊ የቀብር አስፈፃሚ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የተለያየ ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ስነስርዓት የመንግስት ከፍተኛ ባላስልጣናት ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት አዲስ አበባ በሚገኘው በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር እሁድ ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ በ9 ሰዓት እንደሚፈጸም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ምክር ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረትም የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብ ር ስነ ስርዓት በወታራዊ አጀብ የሚከናወን ይሆናል።

 የአንድ ቀን ብሄራዊ የሀዘን ቀን በቀጣይ በሚሰጥ ውሳኔ በመላ ሃገሪቱ እንዲታወጅ ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ግብአተ መሬቱ ከመፈጸሙ በፊት ነገ ቅዳሜ ከንጋቱ 11 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ቤተሰቦችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት የአስከሬን አቀባበል ያደርጋሉ።

በመቀጠል እሁድ ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ እስከ 5 ሰዓት ከ30  በሆስፒታልና በመኖሪያ ቤታቸው የተለያየ ዝግጅት ይካሄዳል።

ከረፋዱ 5 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ጀምሮ እስከ 8 ሰዓት ድረስ በሚሊኒየም አዳራሽ ይፋዊ የአስከሬን አሸኛኘት ስነ ስርዓት እንደሚደረግም ተገልጿል።

አስከሬኑ ከቀኑ  8 ሰዓት አንስቶ ከሚሊኒየም አዳራሽ ተነስቶ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ይደርሳል።

በመጨረሻም በመካነ መቃብር ስፍራው የሚካሄዱ ዝግጀቶች ሲጠናቀቁ  9 ሰዓት ላይ ግብዓተ መሬት እንደሚፈጸም ከወጣው መርሃ ግብር ማወቅ ተችሏል።።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም