በሚሌኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ ቻይና ንግድ ትርዒት ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
በሚሌኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ ቻይና ንግድ ትርዒት ተከፈተ
በኢትዮጵያ ለሶስተኛ ጊዜ የኢትዮጵያና ቻይና ንግድ ትርዒት በሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ ተከፈተ።
በኢትዮጵያ ለ3ኛ ጊዜ የተከፈተው የንግድ ትርዒት ነጋዴውን ከቻይና አምራቾችና አቅራቢዎች ጋር በቀጥታ በማገናኘት የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል መድረክ ነው።
የአገሪቷን ንግድና ኢንቨስትመንት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር ከሚያስችሉ ኩነቶች መካከል ተጠቃሽ ከመሆኑም ባሻገር ለአምራች ኩባንያዎች ልምድ በማካፈልና ተወዳዳሪነት በማሳደግ የዜጎችን የስራ ዕድል እንደሚያሰፋ ተነግሯል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋናው አርጋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የትርዒቱ መከፈት የሁለትዮሽ ትብብርን ያሰፋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኢኮኖሚክ ካውንስል ሚስተር ዚያ ቲና እንደተናገሩት፤ የንግድ ትርዒቱ የአገሮቹን ሁለንተናዊ ትብብር ከማጠናከሩም በተጨማሪ ኩባንያዎችን ልምድ በማለዋወጥ ለግሉ ዘርፍ ዕድገት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር እንደገለፁት፤ የኢትዮ ቻይና የንድግ ትስስር በ35 ከመቶ እያደገ ቢሆንም ቻይና ካላት አቅም ጋር ሲነፃፀር ብዙ ይቀራል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከተመዘገቡ 400 የሚደርሱ የቻይና ኩባንያዎች ውስጥ መቶ ሃምሳ ያህሉ ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክተው፤ “ቀሪዎች እንዲጀምሩም የንግድ ትርኢቱ መከፈት እገዛ ያደርጋል” ብለዋል።
በንግድ ትርዒቱ 100 ያህል የቻይና እና አገር በቀል ኩባንያዎች የግንባታ ዕቃዎችን፣ ማሽኖችን፣ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን፣ የሃይልና የብርሃን አምራቾችን እንዲሁም የሞተር ተሽከርካሪዎችንና መለዋጫዎችን ለትዕይንቱ አቅርበዋል።
ዝግጅቱ ከሚያዝያ 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን ለጎብኚዎች በነጻ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
አፍሪካን ከቻይና ጋር ለማስተሳሰር የተዘጋጀው የንግድ ትርኢት በቀጣይም በመካከለኛው ምስራቅ፣ በኬንያ፣ በርዋንዳ፣ በናይጄሪያ፣ በጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሳውዲ አረቢያ እና ሞሮኮ እንደሚካሄድ ታወቋል።