እአአ በ2019/20 ምጣኔ ሃብታቸውን በተፈጥሮ ሃብት ላይ ያልመሰረቱ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ እድገት ይኖራቸዋል- አይኤምኤፍ - ኢዜአ አማርኛ
እአአ በ2019/20 ምጣኔ ሃብታቸውን በተፈጥሮ ሃብት ላይ ያልመሰረቱ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ እድገት ይኖራቸዋል- አይኤምኤፍ
ሚያዝያ 24/2011 እአአ በ2019/20 ምጣኔ ሃብታቸውን በተፈጥሮ ሃብት ላይ ያልመሰረቱ የአፍሪካ አገሮች የተሻለ እድገት እንደሚኖራቸው ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ተነበየ።
አይኤምኤፍ የ2019/20 አህጉራዊ ምጣኔ ሃብት ትንበያን ዛሬ ይፋ ሲያደርግ የተሻለ የምጣኔ ሃብት መነቃቃት ከሚኖራቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና እንደምትቀጥል ገልጿል።
ኢትዮጵያ 7 ነጥብ 7 በመቶ እድገት እንደሚኖራት አይኤምኤፍ ግምቱን አስቀምጧል።
ምጣኔ ሃብታቸው በተፈጥሮ ሃብት ላይ ያልተመሰረተ አገሮች ነዳጅን ጨምሮ ኢኮኖሚያቸው በተፈጥሮ ሃብት ላይ ከተመሰረተ አገሮች የተሻለ እድገት እንደሚኖራቸውም አመልክቷል።
ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የምጣኔ ሃብት መነቃቃት እንደሚቀጥል የሚያስቀምጠው ሪፖርቱ አጠቃላይ እድገቱ በ2018 ከነበረው 3 በመቶ ወደ 5 በመቶና ከዚያ በላይ ከፍ እንደሚል ግምቱን አስቀምጧል።
ትንበያው እንደሚያሳየው ኢኮኖሚያቸው በተፈጥሮ ሃብት ላይ ያልተመሰረተ አገሮች ፈጣን እድገት የሚኖራቸው ሲሆን በ2019/20 በአማካኝ 6 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንደሚኖራቸውና የነፍ ወከፍ ገቢያቸው በተሻለ ሁኔታ እንደሚጨምር አስቀምጧል።
በአለም የገንዘብ ድርጅት ምክትል የክፍል ሃላፊ ሚስተር ፓፓ ዲያዬ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢኮኖሚያቸው በተፈጥሮ ሃብት ላይ ከተመሰረተ አገሮች በተሻለ እድገት ይኖራቸዋል።ኢኮኖሚያቸው በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ 24 የአፍሪካ አገሮች ዝቅተኛ እድገት የሚኖራችው ሲሆን ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናቸው።
ሃላፊው እንደሚሉት፤ የአፍሪካ አገሮች እድገት በመንግስት ግዙፍ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ያስፈልጋል።
በቀጠናው የዋጋ ግሽበት ባለፈው አመት ከነበረው 8 ነጥብ 5 ወደ 8 ነጥብ 1 ዝቅ እንደሚል አይኤምኤፍ አመላክቷል።
ሪፖርቱ እንደሚያስቀምጠው የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ሲል በመንግስት ብቻ ተይዘው የነበሩ ተቋማት ውስጥ የግሉ ዘርፍ እንዲገባ ለማድረግ የጀመረውን ተግባር በትክክል ከተገበረ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል።
የሸቀጦች ዋጋ መጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ፣ ግጭትና ሌሎችን ተቋሙ እንደ ስጋት ያስቀመጠ ሲሆን መንግስታት መፍትሔ እንዲፈልጉ ምክረ ሃሳቡን ሰጥቷል።