ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ ይገዙ ዳባ የምርመራ መዝገብ 10 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መሰረተ

ሚያዝያ 24 / 2011 ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ ይገዙ ዳባ የምርመራ መዝገብ 10 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መሰረተ።

ተከሳሾቹ ከ3 ሳምንት በፊት በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት በዛሬው ውሎው ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያጠናቀረውን የምርመራ መዝገብ ተረክቧል።

ተጠርጣሪዎቹ ከ2010 እስከ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መንግስት ለገበያ ማረጋጊያ በፈጸመው አለም አቀፍ የስንዴ ግዥ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ወይም ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ለተባለ ተቋም ጥቅም ለማስገኘት ወይም በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ሊጠብቁትና ሊከላከሉለት የሚገባቸውን በመተላለፍ የመንግስትን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር መፈጸማቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።

''በዚህም በመንግስት ላይ 24 ሚሊዮን ዶላር ወይም 600 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ጉዳት አድርሰዋል ይላል'' ክሱ።

ተከሳሾቹ ''ዐቃቤ ህግ ክስ በመመስረቱ ከዚህ በኋላ የሚጠፋ ማስረጃ ስለሌለ በውጭ ሆነን ጉዳያችንን እንድንከታተል ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ይፍቀድልን'' በማለት ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾቹ የፈጸሙት ወንጀል ከ11 አመት በላይ የሚያስቀጣና ከባድ የሙስና ወንጀል በመሆኑ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲሆን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ካደመጠ በኋላ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።

ከተከሳሾቹ መካከል 1ኛ ይገዙ ዳባ፣ 4ኛ ሰለሞን በትረ እና 10ኛ ጆንሴ ደገፉ ተከሳሾች የግል ጠበቃ ለማቆም አቅም የሌላቸው መሆኑን በመግለጽ መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ መንግስት ጠበቃ ቢያቆምላቸው ተቃውሞ እንደሌለው አስታውቋል።

ፍርድ ቤቱም መንግስት ለተከሳሾቹ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ትዕዛዝ አስተላለፏል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ከሌላቸው ደግሞ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ መዝገቡ ለግንቦት 6 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በእነ አቶ ይገዙ ዳባ የምርመራ መዝገብ ክስ የቀረባቸው ተከሳሾች 1ኛ አቶ ይገዙ ዳባ፣ 2ኛ አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ፣ 3ኛ አቶ መንግስቱ ከበደ፣ 4ኛ አቶ ሰለሞን በትረ፣ 5ኛ ሰለሞን አይኒማዕር፣ 6ኛ አቶ ዮሴፍ ራሲሶ፣ 7ኛ አቶ ተክለብርሃን ገብረመስቀል፣ 8ኛ አቶ ትሩፋት ነጋሽ፣ 9ኛ አቶ ዘሪሁን ስለሺ እና 10ኛ አቶ ጆንሴ ደገፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም