ቀጥታ፡

የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመቀነስ ነጻነት ሳይጎዳ መፍትሄ ማበጀት ይገባል - ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

የአዲስ አበባ   ሚያዝያ  24/2011 የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመቀነስ የመናገር ነጻነት በማይጋፋ መልኩ መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቷ ዛሬ 26ኛው ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን በአዲስ አበባ ሲከበር ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በዘርፉ ባለፈው አንድ ዓመት ያስመዘገበችው ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

ስኬቱ የተገኘው መንግሥት የታሰሩ ጋዜጠኞን ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን በመፍታትና የዘርፉን ሕግ ለማሻሻል በርካታ ሥራ በመስራቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ አገሪቱ ቀድማ በዘርፉ ከምትታወቅበት ሁኔታ እጅግ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና ይህም በዓለም አቀፍ መመዘኛም ጭምር የተረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙሃን በመጣው ለውጥ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ መከበሩን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቷ ''ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት ይበልጥ እንዲሰራ ያበረታታዋል'' ብለዋል።

ዴሞክራሲን ለማጎልበት፣ የሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ፣ የመናገር ነጻነትን ለማስፋትና የዘርፉን አሳሪ ሕጎች ጫና ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት መካሄዱ በሚቀጥለው ዓመት በአገሪቱ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ግብዓት እንደሚሆንም ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙኃን ኅብረተሰቡን በማንቃትና ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ድምጽ በመሆን የሚያገለግል በመሆናቸው በምርጫው ሂደት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያ የሓሰት መረጃዎች እየተላለፉ መሆኑንና ይህም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ስለመሆኑ ገልጸው ጠንካራ ተቋማትና ባለሙያ እጥረት በሆነበት አፍሪካ የሃሰት መረጃን ከእውነተኛው መለየት አዳጋች ስለሚሆን ችግሩ የከፋ ጉዳት እያስከተለ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመቀነስ የመናገር ነጻነትን በማይጋፋ መልኩ መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ነው ፕሬዝዳንቷ ማሳሰቢያ የሰጡት።

ለዚህም ደግሞ በመንግሥታትና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መካከል ተከታታይ ውይይቶች ማድረግ እንደሚገባ ነው እንደ ምክረ ሃሳብ ያስቀመጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም