የሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ቀጣይ ሂደቶችን ህዝበ ሙስሊሙና ታዳሚው እንዲያውቃቸው ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ቀጣይ ሂደቶችን ህዝበ ሙስሊሙና ታዳሚው እንዲያውቃቸው ያደርጋል
የአዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2011 ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ የሰነድ ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ ህዝበ ሙስሊሙና ታዳሚው እንዲያውቃቸው የሚያደርግ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ትናንት በአዲስ አበባ ባካሄደው የውይይት መድረክ ጊዜያዊ የዑለማዎች አጋዥ ምክር ቤት በማቋቋም ጊዜያዊ አጋዥ የቦርድ አባላትንም መርጧል።
ኮሚቴው ያዘጋጃቸውን ሰንዶች፣ ሕጎች፣ መተዳዳሪያ ደንቦች ለጉባዔው በማቅረብ ውይይት ተደርጎባቸው ስምምነት ላይ መደረሱም ይታወቃል።
ኮሚቴው ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው የፌደራል መጅሊሱንም ሆነ የክልልመጅሊሶችን ሃላፊነት በጊዜያዊነት የሚረከቡ፣ የመጅሊሱንም የእለት ከእለት ተግባራት የሚያስፈጽሙ ጊዜያዊ የኡለማዎች ኮሚቴና እነሱን በተግባር የሚያግዝ የቴክኒክ ቡድን ማደራጀቱን ጠቅሷል።
ይህንን ተከትሎ የሰነድ ውይይቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ታዳሚውና ህዝበ ሙስሊሙ እንዲያውቀው የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል።
የኮሚቴውን የውሳኔ ትክክለኛነት የሚጠራጠሩ ወንድሞችና እህቶች ቢኖሩ እንኳ ሁሉም ወገኖቻችን በመሆናቸው እንዲሁም የዲኑ የአሁንም ሆነ መጻኢ እድል የሚያሳስባቸው ናቸው ብለን ስለምናምን ልናግባባቸው የምንችልበት እድል እንዳለ እናምናለን ብሏል።
ኮሚቴው በምንም መልኩ ልዩነትን ተቋማዊ አድርጎ እንደማንሄድ ቃል በመግባት፤ "እኛን የሚተካው አካልም በዚሁ አቅጣጫ እንደሚጓዝ እምነታችን ነው" ብለዋል፡፡
"ማኅበረሰባችን በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ረገድ እየተከተለው ያለው ሥነ ምግባር ከገንቢነት ወደ አፍራሽነት እያሻቀበ በመሆኑና ቅራኔዎችንም እያባባሰ በመሆኑ የህብረተሰቡቡ መሪዎች ይብቃ ሊሉ ይገባ" ብሏልል፡፡
በመጨረሻም "እኛም የሀገራችንን ሰላምና ልማት ይበልጥ የማስጠበቅ ሀላፊነታችንን እንደምንወጣ በህዝበ ሙስሊሙ ስም ቃል እንገባለን" ብሏል፡፡
ኮሚቴው በተለይ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በመጅሊስ የአሰራር ሂደትና ሚና ላይ የተነሳውን ተቃውሞና የለውጥ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ የተቋቋመ መሆኑ ይታወሳል።