የህግ ታራሚዎችና የተጠርጣሪዎች አያያዝ እየተሻሻለ ነው-የሰብአዊ መብት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የህግ ታራሚዎችና የተጠርጣሪዎች አያያዝ እየተሻሻለ ነው-የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
አዳማ ሚያዝያ 24 / 2011ዓ.ም በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያዎች የህግ ታራሚዎችና የተጠርጣሪዎች አያያዝ እየተሻሻለ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በ40 ማረሚያ ቤቶችና በ16 የፖሊስ ጣቢያዎች በህግ ተራሚዎችና በተጠርጣሪዎች አያያዝና በሚያገኙት አገልግሎት ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ማከናወኑን ገልጿል።
በክትትልና ቁጥጥር ግኝት ሪፖርት ዙሪያ ዛሬ በአዳማ ከተማ ውይይት ሲካሄድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸት ገብሬ እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጡ ከተጀመረ ወዲህ በአብዛኛው ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎችና የህግ ታራሚዎች አያያዝ እየተሻሻለ መጥቷል ።
ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በህግ ከለላ ሥር የሚገኙ ዜጎች ህገ- መንግስቱ የሰጠው መብት እንዲከበርላቸው ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል ።
"ይህንኑ ተከትሎ በተቋማቱ በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝና የሚያገኙት አገልግሎት ተሻሽሏል "ብለዋል ።
"ከለውጡ በፊት በታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች ላይ የህግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፀም ነበር" ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ መንግስት በተለይ በማረሚያ ቤቶች ሪፎርም ውስጥ እንዲገቡ ባሳየው ቁርጠኝነት በአብዛኛዎቹ መሰረታዊ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተቋማቱ ለወጦች ቢኖሩም በማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ያሉባቸው ችግሮች ተለይተው ለፖሊሲ አውጪዎችና አስፈፃሚዎች መላካቸውን ጠቁመዋል።
በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ጥበቃና ክትትል ዳይሬክተር አቶ አድሐም ዱሪ ባቀረቡት የግኝት ሪፖርት ከለውጡ ወዲህ የህግ ታራሚዎች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብትና በሚያገኙት ማህበራዊ አገልግሎቶች መሻሻሎች መታየታቸውን ገልፀዋል።
በትግራይ፣ኦሮሚያ፣አማራና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 40 ማረሚያ ቤቶችና 16 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር በ35ቱ መሻሻልሎች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።
ታራሚዎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በማክበርና በማስከበር ኦሮሚያ ክልል የተሻለ አፈፃፀም ማሳየቱን አመላክተዋል።
አምስት ማረሚያ ቤቶች በምግብ፣ በጤና፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በመኝታ አገልግሎት አሰጣጥ የከፋ ችግር ያለባቸው በመሆኑ እንዲዘጉ ምክረ ሃሳብ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
ሪፖርቱ ለመንግስትና አስፈፃሚ አካላት መላኩን የገለፁት ዳይሬክተሩ ቁጥጥር በተደረገባቸው ሁሉም ተቋማት ላይ ከአራት ወር በኋላ ዳግም የማረጋገጫ ስራ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል ።
በውይይቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ዳኞችና የፖሊስ መኮንኖች ተሳትፈዋል።