የቀድሞው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ አስከሬን ቅዳሜ ማለዳ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል - አስተባባሪ ኮሚቴው

85

አዲስ አበባ   ሚያዝያ  24/2011 የቀድሞው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ አስከሬን ቅዳሜ ማለዳ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ የቀብር ስነ ስርአት ክንውን ብሄራዊ ኮሚቴ አስታወቀ።

በአስከሬኑ የአቀባበል ስነ ስርአት ላይ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንደሚገኙ የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

አስከሬኑ ቅዳሜ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሃያት ሆስፒታል ሄዶ የሚያድር ሲሆን እሁድ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንደሚንቀሳቀስ ተጠቁሟል።

የቀብር ስነ ስርአቱ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ለአገራቸው ያገለገሉበትን ክብር በሚመጥን መልኩ በርካታ ስነስረአት እንደሚኖረው የተነገረ ሲሆን እሁድ 4 ሰአት ከ30 ወደ ሚሌኒየም አዳራሽ ተመልሶ የሳቸውን ህልፈት በተመለከተ የሚቀርቡ የተለያዩ መንፈሳዊና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው መልዕክቶች የሚተላለፍበት ስነ ስርዓት ይከናወናል።

ማንኛውም የሃዘኑ ተካፋይ በሚሌኒየም አዳራሽ መገኘት እንደሚችልና ምንም አይነት መግቢያ እንደማይጠየቅም ብሄራዊ ኮሚቴው አስታውቋል።

በዚህም መሰረት እሁድ ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር 9 ሰዓት ላይ የቀብር ስነ ስርዓቱ ይካሄዳል።

ስነ ስርአቱን አስመልክቶ የሚዘጉ መንገዶችና የፀጥታ ጉዳዮች በቀሩት ቀናት ውስጥ እንደሚገለጽ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም