ቀጥታ፡

በባሌ ህፃናትን ከፖሊዮ በሽታ ለመከላከል ክትባት በዘመቻ እየተሰጠ ነው

ሚያዝያ 12/2011 በባሌ ዞን ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ላላቸው ህጻናትን ከፖሊዮ በሽታ ለመከላከል የቤት ለቤት ክትባት እየተሰጠ ነው፡፡

የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ቶሎሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ክትባቱ ከሚያዝያ 22/ 2011ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት በ18 ወረዳዎች ውስጥ ይሰጣል፡፡

በክትባቱ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ላላቸው 300 ሺህ ያህል ህጻናትን ነው ሽፋን ለመስጠት የታቀደው።

 ከ2 ሺህ የሚበልጡ ባለሙያዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና መንገድ መሪዎች ተሰማርተዋል።

አቶ እሸቱ “በየደረጃው በሚገኙ የጤና ተቋማትና ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ የክትባት አገልግሎቱን ተደራሽ ይደረጋል” ብለዋል ።

 የክትባቱ ዓላማ ከጎረቤት ሀገራት ድንበር አካባቢ ሊገባ የሚችለውን የልጅነት ልምሻ በሽታ አስቀድሞ ለመከላከል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከክትባቱ በተጓዳኝ በዞኑ ቤት ለቤት በሚደረገው ዘመቻ የአካባቢው ማህበረሰብ የጤና ዳሰሳ በማድረግ የህክምና አገልግሎት የሚፈልጉት ወደ ጤና ተቋማት መጥተው አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረገል ተብሏል፡፡

እንደዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ገለጻ ለክትባቱ ዘመቻ መሳካት የዓለም ጤና ድርጅት፣  መንግስታዊና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የመድኃኒትና ተጓዳኝ ድጋፍ አድርገዋል።

ለክትባቱ የሚያስፈልገው ቁሳቁስና የሰው ኃይል በሁሉም ቦታ መሟላቱና  ህብረተሰቡም ልጆቹን በወቅቱ በማስከተብ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጎባ ከተማ የምስራቅ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሙንተሃ ሁሴን በሰጡት አስተያየት ” በየጊዜው በሚሰጠው የክትባት አገልግሎት ልጆቼን ከበሽታ መከላከል ችያለሁ ” ብለዋል፡፡

መንግስት በነጻ የሚሰጠው የክትባት አገልግሎት ልጆቻቸውን ከበሽታው ስጋት ነፃ እንዳደረጋቸው የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ዘለቃሽ መንግስቱ  የተባሉት የዚሁ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡

አሁንም  ክትባት እንደሚሰጥ አስቀድሞ ቅስቀሳ በመደረጉ ን ልጆቻቸውን ለማስከተብ  መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በባሌ ዞን ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው  አንድ ሚሊዮን 800ሺህ ህዝብ ውስጥ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት 16 ነጥብ 4 በመቶውን እንደሚሽፍኑ ከዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም