ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የምጣኔ ኃብት የለውጥ ሥራ ለማገዝ የዓለም ባንክ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2011 በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የምጣኔ ኃብት የለውጥ ሥራ ስኬታማ ለማድረግ የዓለም ባንክ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባንኩ ፕሬዚዳንት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ የሚበረታታ የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ አድርጋለች።

በግብርና፣ በኃይል፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚካሄዱት የለውጥ ሥራዎች አዎንታዊ አበርክቷቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያደረገችው እርቀ ሠላም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው የተሻለ የኑሮ ደረጃ ለመፍጠር ይረዳል ነው ያሉት።

የዓለም ባንክም ለውጡን በአድናቆት እየተመለከተው መሆኑን ገልጸው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የምጣኔ ኃብት ማሻሻያዎች ለማገዝ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውም ባንኩ ለኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት የማሻሻያ ሥራዎች ስኬት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው ቆይታም ስለዚሁ የለውጥ ሥራዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ባንኩ በኢትዮጵያ በቢሊዮን ዶላር የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ እየደገፈ መሆኑን ለበጀትም የቀጥታ ድጋፍ እየደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በሥራ እድል ፈጠራ ለማስፋት፣ የኢንቨስትመንት ሥራ ለማሳለጥና የግል ዘርፍ ተሳትፎን ለማሳደግ ባንኩ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ለውጥም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ አገራትም ጭምር ትሩፋት እንዲኖረው በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም የለውጥ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሎ ለአካባቢው አገራት ምሳሌ በሚሆን መልኩ የዓለም ባንክ ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱንም አስረድተዋል።

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳን ዴቪድ ማልፓስ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ሞዛምቢክና ግብጽ ያቀናሉ።

የዓለም ባንክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ 1945 ነበር የተቋቋመው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም