የምዕራብ ኦሞ ዞን ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ ኦሞ ዞን ተመሰረተ
ሚያዝያ 23/2011የቀድሞ የቤንች ማጂ ዞን ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ በሚል በሁለት ዞን በአዲስ መልክ እንዲደራጅ በክልሉ ምክር ቤት የተላለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ዞኑ በይፋ ተመሰረተ።
ዛሬ የተመሰረተው የምዕራብ ኦሞ ዞን አምስት ነባርና ሁለት አዳዲስ ወረዳዎችን በማቀፍ በሰባት ወረዳዎች እንዲዋቀር ተደርጓል።
በምስረታው መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የደኢህዴን ተወካይና የክልሉ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም የደቡብ ክልል ምክር ቤት 44 አዳዲስ ወረዳዎችና ሶስት ዞኖች በአዲስ እንዲደራጁ መወሰኑን አስታውሰዋል።
የቀድሞ የቤንች ማጂ ዞንም በአዲስ ከተዋቀሩት ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
"በዞኖቹ የመዋቅር ተገቢነት ላይ ጥናት ተደርጎ አዳዲሶቹ ዞኖች በይፋ ስራ እንዲጀምሩ በተላለፈ ውሳኔ መሰረት ዞኑ በይፋ ተመስርቷል"ብለዋል።
"መዋቅር ብቻውን ግብ አይደለም" ያሉት አቶ ክፍሌ የአካባቢ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ለዞን ምስረታ ተተኳሪ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
"የዞን ምስረታውን ተከትሎ ባለፉት ዓመታት ሳይፈታ ለዘለቀው የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ክፍሌ የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም ዞኑን የልማት ቀጠና ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ዞኑ በሰላምና በልማት የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ክፍሌ አስታውቀዋል ።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን የተሾሙት አቶ ፋጂዎ ሳፒ የዞን የመዋቅር ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄ መቅረቡን አስታውሰዋል ።
የአካባቢው ማህብረሰብ እስከ ምሰረታው ላሳየው ሰላማዊ እንቅሰቃሴም ምስጋና አቅርበዋል ።
የአካባቢው የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አቶ ፋጂዎ አስታውቀዋል ።