ቀጥታ፡

ኢሠማኮ የሰራተኞች የመነሻ ደመወዝ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠየቀ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2011 የሰራተኞችን የመነሻ ደመወዝ በመንግስት በኩል ውሳኔ እንዲሰጥበት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ጠየቀ።

ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ዛሬ በኢትዮጵያ ሲከበር የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንደገለጹት ፤ ሰራተኛው ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉት።

ስለሆነም መንግስት የኮንፌዴሬሽኑ አባል ሰራተኞች የመነሻ ደመወዝ ኑሯቸውን ማሻሻል በሚያስችል ደረጃ እንዲስተካከል ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤ ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መንግስት የመነሻ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ጠይቀዋል።

"መግስት የዜጎች ኑሮ እንዲሻሻልና ድህነትን ለመቅረፍ የስራ ዕድል እየፈጠረ ቢሆንም በተፈጠረው የስራ ዕድል ጉርሳቸውን የማይሸፍኑ ከድህነት ወለል በታች የደሃ ደሃ ሆነው የሚኖሩ ናቸው ስለሆነም መግስት ዜጎች በአገራቸው ሰርተው መኖር እንዲችሉና የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም ተፈጥሮ ምርታማነት አድጎ ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መነሻ የደሞዝ ወለል እንዲወሰን አጥብቀን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

ከመነሻ ደመወዝ በተጨማሪ ሰራተኞች ለመደራጀት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አንዳድ አሰሪዎች ሰራተኞችን ከስራ በማባረርና በማዘዋወር ጫና እንዳያሳድሩ የሰራተኞች በነጻ የመደራጀትና የመደራደር መብትም እንዲከበር ጠይቀዋል።

የሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲጠበቅ፣ ህገ ወጥ ደላሎች ከህገ ወጥ ስራቸው እንዲቆጠቡ፣ የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ሲያደርጉ ዜጎች የስራ እድል እንዲያገኙ መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ካሳሁን አክለዋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የሰራተኞች መደራጀት ጥያቄ ጆሮ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል።

"ስለ ሰራተኛው መደራጀት የተላለፈው መልዕክት ጆሮ ሊሰጠውና ተግባራዊ ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ነው። የሰራተኛው በሰራተኛ ማህበር መደራጀት ሰራተኛውን ብቻ ሳይሆን አሰሪውንና መንግስትን ከፍ ባለ ደረጃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማስተዋል ይገባል። የሰራተኛም ሆነ የአሰሪ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ በስራው ዓለም ውስጥ ማህበራዊ ምክክር ባህል እንዲሆንና የኢንዱስትሪ ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን ያስችላል "

የአዲስ አበባ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው፣ መልካም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት እንዲኖር መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።

የስራ ቦታዎች ለሰራተኞች ጤናና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት የተሟላ የአደጋ መከላከያ ቁሳቁሶች እንዲኖሩና የሰራተኛውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዓለም የሰራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰራተኞች በየአገሮቻቸው የመብትና ጥቅም ጥያቄዎቻቸውን በአደባባይ ወጥተው ለማስተጋባት የሚያከብሩት እለት ነው ።

ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን ''ሜይ ዴይ'' ዛሬ በኢትዮጵያ ለ44ተኛ ጊዜ በዓለም ደግሞ ለ130ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም