ጠበቆች የስነ ምግባር መርሆዎችን ተከትለው በመስራት የዜጎች እርካታን ለማምጣት መስራት ይኖርባቸዋል-የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ - ኢዜአ አማርኛ
ጠበቆች የስነ ምግባር መርሆዎችን ተከትለው በመስራት የዜጎች እርካታን ለማምጣት መስራት ይኖርባቸዋል-የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 23/2011 ጠበቆች የስነ ምግባር መርሆዎችን ተከትለው በመስራት የዜጎች እርካታን ለማምጣት መስራት እንደሚገባቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አሳሰበ።
ጠበቆች በአገሪቷ እየተካሄደ ባለው የፍትህ ዘርፍ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ላይ መጫወት በሚገባቸው ሚና ላይ ከጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጋር መክረዋል።
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጠበቆች አስተዳደር አዋጅንም ማሻሻል የሚቻልባቸው ጉዳዮችም የውይይቱ የትኩረት ነጥብ ነበር።
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በአዲስ አበባና ዙሪያው ከሚገኙ የፌደራል ፍርድ ቤቶችና ጠበቆች ጋር ነው ውይይቱን ያከናወነው።
በዚህም በአገሪቷ በፍትህ መስክ እየተደረጉ ያሉ የማሻሻያ ስራዎች፣የደረሱበት ደረጃና ፈተናዎች ላይ የሚያጠነጥኑ የመወያያ ጽሁፎች ቀርበው ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የፍትህ ስርዓቱን ለመለወጥና ዜጎች በፍትህ አካላቱ ላይ ያላቸውን አመኔታ ለመመለስ ጠበቆች ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ።
የዜጎችን እምነት ለመመለስና የተገልጋይ እርካታን ለመፍጠር ጠበቆች የሙያ ስነምግባርን አክብረው ሊሰሩ እንደሚገባ የጠቆሙት ዶክተር ጌዲዮን፤ ለዚህም የአገሪቷን ሕግ አክብሮ መሄድ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አንድ ጠበቃ ብቻውን ሕግን ጠብቆ አገልግሎት ቢሰጥ ውጤት አይመጣም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ከጎናችን ያለ ጠበቃ ህገ ወጥ ስራ ሲሰራ ስናይ መምከር፣ መገሰጽና ሲያልፍም መጠቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
እንደ ዶክተር ጌዲዮን ገለጻ በምንሰጠው አገልግሎት ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ አሰራራችንን መፈተሽና ማስተካከል ተገቢ ነው።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መታሰቢያ ኃይሉ በበኩላቸው የስነ ምግባር አተገባበር ላይ ችግሮች እንዳሉ ይገልጻሉ።
የስነ ምግባር ህጉ ተፈጻሚ የሚሆነው ፍቃድ ወስደው በሚሰሩ ጠበቆች ላይ ብቻ ነው፤ህጋዊ ሳይሆኑ የሚንቀሳቀሱ ጠበቆች በስነ ምግባር ችግሮች እየተጠየቁ አይደለም ሲሉም ያለውን ችግር ያስረዳሉ።
አቶ መታሰቢያ እንደሚገልጹት በ2009 ዓ.ም 40 በመቶ የሚሆነው የስነ ምግባር ክስ ፍቃድ አለማሳደስ በሚል ነው፤ በ2010 ደግሞ 50 በመቶ እንዲሁም በ2011 ዓ.ም 53 በመቶ የሚሆነው የስነ ምግባር ክስ ፍቃድ አለማሳደስ ነው።
ይህ አሃዝ ከፍተኛ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ፍቃድ ማሳደስ ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን ለማቃለል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ሊደግፈን ይገባል የሚል ሀሳብ አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የስነ ምግባር ክስ አቀራረብና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ተገቢው ፍተሻ ማድረግ ይገባል የሚል አስተያየትንም አንስተዋል።
በተለይም የጠበቆች የስነ ምግባር ህጉ ለሁሉም ተደራሽ አይደለም የሚል ሀሳብ የተንጸባረቀ ሲሆን ህጉን ሁሉም ጠበቃ እንዲያውቀው በማድረጉ ላይ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
ከውይይቱ ታሳታፊዎች መካከል ጠበቃ አበበ ጉታ በሰጡት አስተያየት ''እኛ የእናንተ ነጻብራቅ ነን፤ የእናንተ ስነ ምግባር ሲልቅ የጠበቆችም ይልቃል" ነው ያሉት።
ሀኪም የውሸት መድሃኒት እንዳማያዝ ሁሉ እኛም የውሸት ጥብቃና አንቆምም፤ አቃቤ ህግም የውሸት ክስ መመስረ የለበትም ሲሉም ተደምጠዋል።