ኮለኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበላይነት እየመራች ትቀጥላለች ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ኮለኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበላይነት እየመራች ትቀጥላለች ተባለ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 23/2011 ኮለኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ መጪው ዓመት የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በበላይነት እንደትምትመራ ተገለጸ።
ከወራት በፊት ፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በሁለት ወራት ውስጥ በመጥራት የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንት ይመርጣል የተባለው በስህተት መሆኑም ተገልጿል።
ሻለቃ ኋይሌ ገብረስላሴ ከአምስት ወራት በፊት ህዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም ሁለት ዓመት የስልጣን ጊዜ እየቀረው ራሱን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት ማግለሉን ተከትሎ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ህዳር 5 ቀን 2011ዓ.ም በጊዜዊነት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።
በወቅቱም በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ለቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንት የሚመራ አካል እንደሚያስመርጥ ነበር የተገለጸው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ ማቆያ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮለኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ እስከ መጪው ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በበላይነት እየመራች ትቆያለች ብለዋል።
መመሪያው ላይ የፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ስልጣኑን ቢለቅ ማን እንደሚተካውና ምርጫው በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት የሚያስቀምጠው ነገር የለም።
ይሁን እንጂ በቀጣይ ይሄን ማስተካከል እንደሚገባ ነው አቶ ቢልልኝ የጠቆሙት።
አሁን በላው ሁኔታ ግን ፕሬዚዳንቱ በድንገት ስልጠኑን ቢለቅ ማን ይተካዋል የሚለው ከሌሎች ፌዴሬሽኖች ላይ ተሞክሮ በመውሰድ እንድትቀጥል ተደርጓል ብለዋል።
ሻለቃ ኋይሌ ገብረስላሴ የስልጣን ማብቂያው ጊዜ ከሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላም ተጨማሪ አንድ ዓመት ስለሚቀረው ፌዴሬሽኑን በባለይነት ማን ይመራው የሚለው በሚቀጥለው ዓመት በሚከናወነው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ የሚወሰን ይሆናልም ብለዋል።
የጉባኤው አባለት ሌላ ሰው እንዲመረጥ ጥያቄ ካላነሱ በቀር ኮለኔል አትሌት ደራረቱ ቱሉ ፌዴሬሽኑን በበላይነት እየመራች የምትቀጥል ይሆናልም ብለዋል።