ቀጥታ፡

ነገ በሚተላለፈው ውሳኔ መሰረት ሃላፊነቴን ለማስረከብ ዝግጁ ነኝ - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት

አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አሚን ጀማል ነገ በሚደረገው የኡላማዎች ጉባኤ በሚተላላፉ ውሳኔዎች መሰረት ሃላፊነታቸውን ለማስረከብ ዝግጁ መሆናችውን ገለጹ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጉባኤ 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ አሚን ጀማል በጤና ችግር ምክንያት ያቀረቡት የስራ መልቀቂያን ሳይቀበል መቅረቱ ይታወሳል።

የመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት እስካሁን በጥሩ መንገድ ሲመሩት የነበረውን ተቋም ምርጫ እስከሚካሄድ አልያም ነገ በሚካሄደው ሀገራዊ ጉባኤ መጅሊሱን የተመለከቱ ውሳኔዎች እስከሚታወቅ በሃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ጠይቆአቸው ነበር።

ሼህ መሀመድ አሚን ጀማልም ትላንት ጉባኤው ያስተላለፋቸውን ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫና የነገውን ጉባኤ አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የስራ መልቀቂያ በተደጋጋሚ ለወከላቸው የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትና ለስራ አስፈጻሚው ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም የመወሰንም ሆነ መልቀቂያውን የመቀበል ሃላፊነትና መብት ያለው ጉባኤው በመሆኑ እረፍት እያደረጉ እንዲሰሩና ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲጠብቁ የጠቅላይ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ በወሰነው መሰረት ትናንት ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ነገ ጉባኤው በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት እሳቸውን ጨምሮ አስራ አንዱ ስራ አስፈጻሚዎች ብቁ ሆኖ ለሚመጣ አመራር ሃላፊነት ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ትናንት የተደረገው ውሳኔ ነገ በሚካሄደው የኡላማዎች ጉባኤ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ለመቀልበስ  የተደረገ አለመሆኑም መታወቅ እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ ሼህ አይዘዲን ሼህ አብዲላዚዝ በበኩላቸው በነገው ጉባኤ "መጅሊሱ ስራ ይልቀቅ" የሚል ውሳኔ ካስተላለፈ ለመልቀቅ ዝግጁ ነን ብለዋል።

በነገው ጉባኤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተቋቋመው ኮሚቴ የተዘጋጀው ሰነድና ሌሎች ሰነዶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

በዚህም ሁሉም ስራ አስፈጻሚ አዲስ ለውጥ ከመጣ እንደሚቀበል በጠቅላላ ጉባኤው አረጋግጧል።

በጉባኤው የአገሪቷ ኡላማዎች የሚሳተፉ ሲሆን ኡላማዎቹም ከየክልሉ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል ተብሏል።

ከየክልሉ የመጡ ኡላማዎች በሰከነና በተረጋገ መንፈስ ውይይቱን እንዲያካሄዱ ተሳታፊዎች እምነታቸውን አክብረው በእርጋታ እንዲያካሂዱ ዋና ጸሃፊው መልክት አስተላልፈዋል።

በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል በሚካሄደው ጉባኤ ከፍተኛ የመንግት ባለስልጣናትን ጨምሮ ጉባኤው የሚመለከታቸው የእምነቱ ተከታዮች ይገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል።

መጪው ጊዜ ረመዳን እንደመሆኑ ሙስሊም ወንድማማቾች አፉ ተባብለው በንጹህ ልቦና በአንድነት ኢባዳውን እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም