ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 22/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ምክንያቶች ከቄዬያቸው ተፈናቅለው በክልሉ መንግስትና በሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት  እርዳታ ሲደረግላቸው ለነበሩ ዜጎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ33 ሚሊዮን 612 ሺህ ብር  አድርጓል።

ድጋፉን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ ከባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና እጅ ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና በዚሁ ወቅት "ግጭቶችና መፈናቀሎች ለዘመናት በመቻቻልና በመተሳሰብ ለኖረች አገራችንና ህዝቦቿ  መገለጫዎች ሊሆኑ አይገባም" በማለት በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው መፈናቀልና በደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ማዘናቸውን አስታውቀዋል ።

ባንኩ የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ  በተለያዩ ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የአጠቃላይ የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ የወሰነውም ከብሄራዊ አደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን ያገኘውን የተፈናቃዮቹን አሃዝ መሰረት በማድረግ ሲሆን፣ የዛሬው ድጋፍም ባለው የተፈናቃዮች አሃዝ የተሰጠው የኦሮሚያ ድርሻ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያበረከተውን ድጋፍ ማድነቃቸውን ገልጸው ሌሎችም ተቋማትና ግለሰቦች ይህን በጎ ተግባር በአርአያነት በመውሰድ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለመቋቋም ሊተባበሩ እንደሚገባ አንስተዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አጠቃላይ ሁኔታና በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት "በአንድ አገር ውስጥ ያለ የክልሎች ግንኙነት ሳይሆን በተለያዩ አገራት መካከል ያለ ግንኙነት ነው የሚመስለው" በማለት፤ "ልንመሰርታት የምናስባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት ይህ አስተሳሰብ ጋሬጣ ነው የሚሆነው" ብለዋል።

በመሆኑም በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከርና ወደ ቀድሞው ሁኔታ እንዲመለስ፤ መገፋፋትና ውጥረቶች እንዲቀንሱ የክልሉ መንግስት ጠንክሮ ይሰራል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ።

የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቤታቸው እዳይመለሱ ተደራጅተው የሚሰሩ የፖለቲካ ነጋዴዎች እዳሉ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የዜጎች የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት ሙሉ በሙሉ መረጋገጥ ስላለበት የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ  የሚፈጸም ይሆናልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም