ለዶክተር ነጋሶ የቀብር ሥነ ስርዓት ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል - ኢዜአ አማርኛ
ለዶክተር ነጋሶ የቀብር ሥነ ስርዓት ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል
ሚያዝያ 22/2011 ለቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ሥነ ስርዓት ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል።
ለቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ሥነ ስርዓት ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን ገለጸ።
ብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከቤተሰቦቻቸው የተውጣጣ ነው ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታና የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንዳሉት፤ የዶክተር ነጋሶን የቀብር ስነ ስርአት ለማስፍፀም ኮሚቴው ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል።
ኮሚቴው በስሩ ሶስት ንዑሳን ኮሚቴዎች፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ የዝግጅት፣ በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራ የሎጂስቲክስ እንዲሁም የደህንነትና ጥበቃ ኮሚቴዎች ስራቸውን ጀምረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቲካን አያኖ የዶክተር ነጋሶን ህልፈት ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በጀርመን ፍራንክፈርት በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በኩል መስማታቸውን አስታውሰዋል።
ቆንስላው ህክና እያደረጉ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ህይወታቸው ካለፈ በኋላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አስከሬናቸው አስካሁን ሆስፒታል እንዳለ ገልጸው ሆስፒታሉ ምርምራ ጨርሶ መልቀቂያ እንደሰጠ ወደ አገር ቤት ሲገባ አቀባበል ለማድርግ እየተጠበቀ ነው ብለዋል።
እስካሁን ያለን መረጃ "ለህክምና ክትትል ሂደው ህይወታቸው እንዳለፈ ነው" ያሉት አምባሳደር ብርቱካን የሆስቲታሉ ሙሉ መረጃ ሲደርሰን ስለአሟሟታቸው ዝርዝር ሁኔታ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል።
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ርዕስ ብሄር በመሆን አገራቸውን በታታሪነትና በቅንነት አገልግለዋል።
ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ዶክተር ነጋሶ በ1997 ዓ.ም ምርጫ በደንቢ ዶሎ በግል ተወዳድረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ነበር።