ቀጥታ፡

ለልማት ተነሽ ዜጎች የካሳ ክፍያው ጉድለቶች አሉበት ተባለ

አዲስ አበባ ሚያዝያ  22/2011 በልማት ምክንያት ከአካባቢያቸው ለሚነሱ ዜጎች መንግስት ተገቢውን የካሳ ክፍያ በመክፈል በኩል ጉድለቶች ይስተዋሉበታል ተባለ።

በልማት ምክንያት ከአካባቢያቸው ለሚነሱ ዜጎች መንግስት ተገቢውን የካሳ ክፍያ በመክፈል ረገድ ጉድለቶች እንዳሉበት ተገለጸ።

የኢትዮጵያ የመብት ድርጅቶች ህብረት ከአምሃ መኮንን እና ተባባሪዎቹ የህግ ቢሮ ጋር በመተባበር ከልማት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ መፈናቅሎችና ጥሰቶችን በሚያመላክት ጥናት ላይ ከሚመለከታቸው በአለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት የግጭት መንስኤ የሚሆንና ሌብነትን የሚያራባ ሳይሆን ህዝባዊ መሰረት አንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል።

በአዋሳ ዩኑቪርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዳንኤል በሃይሉ እንደገለጹት፤  መንግስት በአሁኑ ወቅት ለልማት ብሎ የሚያፈርሳቸውና ዜጎችን የሚያስነሳበት ሁኔታ ማህበረሰቡን ተጎጂ እያደረገ ነው።

ለከተማ መስፋፋት፣ ለተለያዩ መሰረተ ልማቶች፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለትላልቅ ፕሮጀክቶችና ለሌሎችም ብሎ የሚጠቀማቸው ልማቶች ህብረተሰቡ ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ለአብነትም በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ኦሞ እንዲሁም አዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ላይ “ልማት” በህብረተሰቡ ዘንድ በስጋት እየታየ መሆኑንም ይገልጻሉ።

ከልማት ጋር በተያያዘ እየታዩ ያሉ መፈናቀሎችና ጥሰቶችም አገርን ከማናወጥ ባሻገር በህዝቦች ላይ ግር ግርና ንትርክም እያስነሳ እንደሚገኝም በመጠቆም።

"መንግስት ለልማት ተነሽዎች የሚሰጠው የካሳ ክፍያ ዜጎችን የሚጎዳና የኑሮ መሰረታቸውን የሚያናጋ ነው" ያለት ዶክተር ዳንኤል ይህም ዜጎችን ለአመጽ፣ ሃይልን በመጠቀም መብታቸውን የማስጠበቅ አማራጭ እንዲከተሉ አድርጓቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አጠቃላይ የአገሪቷን የመሬት ፖሊሲና የካሳ ስርአቱን መከለስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ልማት በመንግስት ብቻ ሳይሆን ህዝብን ባማከለ መልኩ በጋራ ምክክርና እቅድ በመፈጸም ህገ መንግስታዊ ጉድለቶችን የሚሞላበትን መንገድ መፍጠርም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በተለይ ክልሎች ወጥና ግልጽ የሆነ መመሪያ ሊኖራቸው ይገባል በማለትም ከውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስቷል።

የአገሪቱንና የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማያጎድል መልኩ በመስራት ለልማት ተነሺዎችም ተመጣጣኝና ፍትሃዊ ካሳ መክፈል ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

"መሬት የህዝብና የመንግስት ነው" የሚለው ሃሳብ ላይም መንግስት ግልጽ የሆነ የአሰራር ስርአት መዘርጋት ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም