ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በእውነትና በፍትህ ላይ የተመሰረተ እርቀ-ሰላም ማምጣት የሚያስችሉ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ለይቻለሁ አለ

ሚያዝያ 22/2011 የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በእውነትና በፍትህ ላይ የተመሰረተ እርቀ-ሰላም ማምጣት የሚያስችሉ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች መለየቱን ገለጸ።

ዜጎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ የባለሙያዎች ቡድን ሊያቋቁም መሆኑንም አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ሁለት ወራት የሆነው ሲሆን ያለፉት ሁለት ወራት የስራ ቆይታውን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌልና ምክትል ሰብሳቢዋ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ናቸው።

ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ እንዳሉት ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሰረት የግጭቶች መሰረታዊ መንስኤ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።

ባለፉት ሁለት ወራትም በፍትህ ላይ የተመሰረተ እርቅ ለማምጣት ጽህፈት ቤት ከማቋቋም ጀምሮ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች መለየቱን አስታውቀዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ የባህላዊ ግጭት አፈታት ላይ የተሰሩ ጥናቶች መፈተሹን ገልጸዋል።

ከአውሮፓ ህብረትና ከተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎች ጋር ኮሚሽኑን ማገዝ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉንም አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ ማንን ከማን ነው የሚያስታርቀው የሚል ጥያቄም ከጋዜጠኞች ተነስቶም ምላሽ ሰጥተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ከ1 ሺ 500 በላይ አቤቱታዎች መቅረባቸውንና ከእነዚህም የእርቀ-ሰላም ኮሚሽኑን ይመለከታል የተባሉ 46 አቤቱታዎችን መለየቱንም ምክትል ሰብሳቢዋ አስረድተዋል።

ይሁንና ኮሚሽኑ የአቤቱታ አቅራቢዎችን ደህንነት የሚያረጋግጡ ህጎችና ደንቦች በማስፈለጋቸው እነዚህን የመለየት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በኩል የቀረቡ አቤቱታዎችን መነሻ በማድረግ ዜጎች እንዲደመጡና ፍትህ እንዲያገኙ የሚያመቻች የባለሙያዎች ቡድን ይቋቋማልም ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ "ኮሚሽኑ ከመንግስት ገለልተኛ ከመሆኑ ባለፈ በጊዜ የተገደበ ስልጣን ያለው መሆኑና ማስረጃን መሰረት በማድረግ ሰዎች የሚደመጡበትን አግባብ መፍጠሩ ከሰላም ሚኒስቴር ይለየዋል"።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም