ቀጥታ፡

ለኦቲዝም ህክምና የሚሰጡ ባለሞያዎች እጥረት ችግር ሆኗል

አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2011ለኦቲዝም ታካሚዎች የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እጥረት እንደገጠመው ኒያ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም ገለፀ።

በኦቲዝም ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኒያ ፋውንዴሽን ለታማሚዎች የህክምናአገልግሎት የሚሰጡ የባለሙያዎች እጥረት እንደገጠመው ገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ከዚህ በፊት ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎች ትኩረት መደረጉ ለችግሩ ምክንያት እንደሆነ 
ተናግሯል።

ኦቲዝም በህፃናት የነርቭና የእድገት ክትትል ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር፤ የመግባባት ችሎታና ክህሎታቸውን የሚጎዳ ወይም የሚቀንስ በሽታ መሆኑ ይነገራል።

ሲዲሲ የተባለው አለም አቀፍ ተቋም እ.አ.አ በ2018 ባወጣው መረጃ መሰረት በአለም ላይ ከ59 ህፃናት አንዱ ለኦቲዝም ህመም ተጋላጭ ይሆናል።

በኢትዮጵያም የኦቲዝም ታማሚ ህፃናት ቁጥር በርከት ያለ እንደሆነ ቢገመትም እስካሁን ግን ትክከለኛውን ቁጥር ማወቅ አልተቻለም።

በሀገሪቱ በኦቲዝም ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ኒያ ፋውንዴሽን ኦቲዝም ያለባቸው ህፃናት የተለያየ ድጋፍ እንዲያገኙ ሲያደርግ መቆየቱን የፋውንዴሽኑ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ኤርሚያስ መኮንን ገልጸዋል።

በስሩ ባለው ጆይ የኦቲዝም ማዕከል በኩልም ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ልዩ ስልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።

እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለፃ 80 ልጆች በማዕከሉ አገልግሎት እያገኙ ቢሆንም የፋይናንስ አቅም ውስኑነትና በአገልግሎት ሰጪ አካላት የሚታይ የግንዛቤ ችግር እንቅፋት ሆኖባቸዋል።

የኦቲዝም ታማሚዎችን የሚያክሙ ባለሙያዎች በተለይም ቴራፒስቶች እጥረትም ሌላው እንቅፋት ሆኗል ይላሉ።

ኦቲዝምን በተመለከተ እንደ አገር የተደራጀ መረጃ ያለመኖሩም ለችግሮች ምላሽ እንዳያገኙ እንከን ሆኗል ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሰው ኃይል ልማት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው ከዚህ በፊት ትኩረት የተሰጠው ለተላላፊ በሽታዎች በመሆኑ ችግር እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ግን ሚኒስቴሩ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎችም ትኩረት ሰጥቶ ባለሙያዎችን የማፍራት ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦቲዝም ላይ የሚያስፈልጉ ቴራፒስቶችንና ሌሎች ባለሙያዎችን ለማሰልጠንም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የዘርፉን ባለሙያዎች ለማሰልጠን እቅድ ተይዟል ብለዋል።

የንግግር (ስፒች ቴራፒ) ስልጠናም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየሰጠ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ለማስፋት መታቀዱን ጠቁመዋል።

እስካሁን በኦቲዝም ታማሚዎች ዙሪያ የተደራጀ መረጃ ባይኖርም በቀጣይ የተደራጀ መረጃ በመያዝ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ በኩል የባለሙያ እጥረት ያለባቸውን የጤና ችግሮች በመለየት ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የሰው ሀብት ልማት ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም