የሰራተኞች ደህንነትና ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብት እንዲጠበቅ መንግስት ሰላምን ማረጋገጥ አለበት-ኢሰማኮ - ኢዜአ አማርኛ
የሰራተኞች ደህንነትና ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብት እንዲጠበቅ መንግስት ሰላምን ማረጋገጥ አለበት-ኢሰማኮ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2011 የሰራተኞች ደህንነትና ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብት እንዲጠበቅ መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ አበክሮ መስራት እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡
ኮንፌዴሬሽኑ ከነገ በስቲያ በኢትዮጵያ ለ44ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ130ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን (ሜይ ደይ) አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ መግለጫ ሰጥቷል።
በዓሉ "ሰላም ለአገር አንድነት፤ ለሰራተኛ መደራጀት እና ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት ነው" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በፓናል ውይይት ይከበራል።
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት መንግስት ባለፈው አንድ ዓመት በፖለቲካው፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በሌሎች መስኮች በርካታ ለውጦችን አድርጓል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሰራተኛው ሰርቶ ለመግባትና ተረጋግቶ ለመስራት እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለመስራት ችግር እየገጠመው እንደሆነ ተናግረዋል።
የጸጥታው ችግር ለሰራተኛው ደህንነትና ዋስትና አስቸጋሪ በመሆኑም መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ አበክሮ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
የአገር አንድነትና የሰራተኛው መደራጀት እንዲሁም ሁለንተናዊ እድገት መምጣት የሚችለው ሰላም ሲፈጠር ብቻ እንደሆነ በማሰብ የኮንፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የዘንድሮው መሪ ቃሉን ሰላም ላይ ያተኮረ እንደሆነ ነው አቶ ካሳሁን ያስረዱት።
ለሰላም መስፈንና ለአገር መረጋጋት ሃላፊነት ያለበት መንግስት ብቻ እንዳልሆነና ሰራተኞችም ለአገራቸው ሰላም መረጋገግጥ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን የሚያከብረው በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ለሰራተኞች መብትና ጥቅም መከበር ሲታገሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ሰራተኞችን ለመዘከርና የትግል እንድነት ቃልኪዳንን እንደገና ለማደስ ነውም ብለዋል።
በተጨማሪም የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ለመንግስት መቅረብ አለባቸው ያሏቸውን "የኢትዮጵያ ሰራተኞች የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን" በመግለጫው ላይ አንስተዋል።
በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች እና በህገ መንግስቱና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እውቅና የተሰጠው የመንግስት ሰራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብት መከበር፣ አገር አቀፍ የመነሻ ደመወዝ ወለል እንዲኖር፣ የስራ ቦታዎች ከአደጋና ከበሽታ የጸዱ እንዲሆኑና የወጡ የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ በተሻለ መልኩ መስራት የኮንፌዴሬሽኑ ዓላማዎች ናቸው።
በሰራተኛ ላብ ምንም ሳይሰሩ የሚነግዱ ኤጀንሲዎች ግን መኖር እንደሌለባቸው አስፈላጊ እርምጃ እንዲወሰድ ከመስራት ባለፈም በኢትዮጵያውያን ሊሸፈኑ የሚችሉ የዝቅተኛ የስራ መደቦች ላይ ብዙ ስራ አጥ ባለበት ሁኔታ የውጭ ዜጎችን መቅጠር እንዲቆምም እንደሚጥር ተገልጿል።
ኮንፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ከማቅረብ ካለፈ የሰራተኞች ጤና ደህነንት መጠበቅ በተለይም የሰራተኞች የስራ ላይ አደጋ ዋሰትና ክፍያ ጉዳይ እንዲሁም እንደ አገር የመነሻ ደመወዝ ወለል የሚያወጣ ምክር ቤት እንዲቋቋም የሚሉ ሀሳቦች በአሰሪና ሰራተኛ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እንዲካተቱ ግፊት አድርጎ ሀሳቦቹ በአዋጁ ውስጥ ተካተው አዋጁ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን አመልክተዋል።
ከፓናል ውይይቶች በተጨማሪ ከመጋቢት 2011 ዓ.ም አንስቶ በጅማ ከተማ 10 የስፖርት አይነቶች ሲካሄዱ የቆዩ ሲሆን የዚሁ አገር አቀፍ የዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን መታሰቢያ ውድድር ማጠቃለያ በዚያው በጅማ እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል።
እግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቼስ፣ ከረንቡላና አትሌቲክስ ከስፖርት አይነቶቹ መካከል ይገኙበታል።
ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) ከእ.አ.አ ግንቦት 01 ቀን 1886 ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን በመላው የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ በርካታ የሠራተኛ ማህበራት በቀን የስምንት ሠዓት የሥራ ሠዓት ስራ ተግባራዊ እንዲሆን በመሻት የሥራ ማቆም እርምጃ ለመውሰድ በመስማማታቸው ምክንያት ችካጎ ላይ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለሞትና ከፍተኛ ጉዳት የተዳረጉበትና በተቃውሞ የተፈለገው የስምንት ሠዓት የሥራ ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገበትን ቀን ለማስታወስ በዓሉ በየዓመቱ ይከበራል።