ቀጥታ፡

መሠረታዊ ነፃነቶችና የብዝኃ ባህል መገለጫዎችን ለማሳደግ የባህል ፖሊሲዎችን መቃኘት በሚል ውይይት ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2011 ኢትዮጵያ በብዝኃ ባህል መገለጫዎች ጥበቃና ልማት ላይ የወጣውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምሕርት፥ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የ2005 ኮንቬንሽን መፈረሟ ለኢኮኖሚና ልማት ስኬት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ “መሠረታዊ ነፃነቶችና የብዝኃ ባህል መገለጫዎችን ለማሳደግ የባህል ፖሊሲዎችን መቃኘት” በሚል መሪ ሐሳብ በነገው ዕለት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ውይይት ያካሂዳል።

ሚኒስቴሩ ውይይቱን የሚያካሂደው በዩኔስኮ ፕሮጀክት ማዕቀፍ ትብብርና  በስዊድን ዓለም ዓቀፍ የልማት ኤጀንሲ/ሲዳ/ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

ውይይቱ ብዝሃ ባህልን መጠበቅና ማበረታታት በሚሉና በሌሎች ርእሶች ላይ ምክክር የሚያደርግም ይሆናል።

በሚኒስቴሩ የባህል፣ የኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክተር አቶ ይስማ ፅጌ ለኢዜአ እንዳሉት አገሪቷ ስምምነቱን የፈረመችው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር  በ2008 ሲሆን ስምምነቱ ለብዝሃ ባህል እድገትና ጥበቃ የማይተካ ሚና ከመጫወቱ ባሻገር እውቅና የሚሰጥም ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በታህሳስ 2016 የኮንቬንሽኑን አፈፃፀም ሪፖርት ለዩኔስኮ ልኳልም ብለዋል።

ሪፖርቱ በሚኒስቴሩ፣ በሌሎች ሚኒስቴችና የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም በፈጠራ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በተሰማሩ ሲቪል ማህበራት ቅንጅት እንዲሁም በዩኔስኮ እገዛና በስዊድን መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።

በሀገሪቷ ብሔራዊ የባህል ፖሊሲና የፊልም ፖሊሲ  በሥራ ላይ መዋል ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፈጠራ ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት ለመደገፍና ለአፈጻጸሙ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አስታውቀዋል።

በዕለቱም "ቅድሚያ ለሀገራዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ መስጠትና አዲሱን የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ወደ ተግባር ማስገባት" በሚል ርዕስ ላይም ውይይት ይካሄዳል ነው ያሉት።

የመስቀል በዓል አከባበር እና የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ የማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው የሚታወስ ሲሆን የጥምቀት በዓል አከባበር፣ ፍቼ ጨምበላላና የአሸንዳ በዓል አከባበርም በዚሁ ዘርፍ ለማስመዝገብ በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም