በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የመመረዝ ህክምና ማእከል የብዙዎችን ህይወት እየታደገ ነው

155
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተቋቋመው የመመረዝ ህክምና ማእከል የብዙዎችን ህይወት እየታደገ መሆኑን ተገለጸ፡፡ ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ የሆነው ወይዘሪት ሃረገወይን አስማማው ከቀናት በፊት በከፋ የጤና ችግር ውስጥ የወደቀውን ወንድሟን ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማስታመም ላይ ናት። በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሆነው ወንሟ ብስራት አስማማው ለዚህ የጤና ችግር የተዳረገው ደግሞ መድሃኒት አብዝቶ በመውሰዱ ምክንያት መሆኑን የህክምና ባለሙያዎቹ እንደነገሯት ትገልፃለች። በዚህም የተነሳ ብስራት በከፋ የመተንፈሻ አካልና የአንጀት ቁስለት መመረዝ ጤናው ታውኮ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ የመመረዝ ወይም የቴክሶሎጂ ህክምና ማእከል በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል እርዳታ እየተደረገለት ነው። አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት የሆነው ይህ የህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ ሲሆን፤ እንደ ብስራት ሁሉ በመድሃኒት መመረዝ ጤናቸው የተጎዳ ከ340 በላይ ለሚሆኑ ህመምተኞች የህክምና አገልግሎት በመስጠት ህይወታቸውን መታደግ መቻሉን ሆስፒታሉ አስታውቋል። የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ያእቆብ አሰማሀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ ከመድሃኒትና ኬሚካሎች መመረዝ ጋር በተያያዘ በሰዎች ጤና ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መጥቷል። በተለይ በሀገሪቷ የሚስተዋለውን የኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች መስፋፋትን ተከትሎም የዚህ ዓይነት የጤና ችግር በዚያው ልክ እየጨመረ መምጣቱንም  ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት። በመመረዝ ሳቢያ ለሚደርሱ የጤና እክሎች ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው ህክምና አሁን ባለው መልኩ ራሱን የቻለና የተደራጀ አልነበረም ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ከመመረዝ ጋር ጉዳት የሚገጥማቸው ህሙናን የሚያገኙት ህክምና "ጊዜያዊ ችግራቸውን የሚያቃልል እንጂ ዘለቄታዊና ቀጣይነት አልነበረውም" ብለዋል። አሁን ላይ  በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተቋቋመው የመመረዝ ህክምና መስጫ ማዕከል  በማንኛውም ዓይነት ከመመረዝ ጋር ንኪኪ ያላቸውን በሽታዎችን በማከም አንድ ዓመት አስቆጥሯል። ማዕከሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለመመረዝ አደጋ የሚዳረጉትን ታማሚዎች ከመርዳት ባለፈ ራሳቸውን በራሳቸው በኬሚካልና መሰል መድሃኒቶች ለመጉዳት ለሚሞክሩ ሰዎችም ከቅድመ ህክምና ጨምሮ ሌሎች ዘላቂ የህክምና አገልግሎቶችንም እንደሚሰጥ የሆስፒታሉ ኃላፊ ተናግረዋል። ወይዘሪት ሃረገወይን እንደምትለው ደግሞ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ እርዳታ አየተደረገለት ያለው ወንድሟ ጤና እየተሻሻለ መጥቷል። በማዕከሉ የሚሰጠው አገልገሎትም የሚያረካ መሆኑን ነው ወይዘሪት ሃረገወይን የተናገረችው። በድንገተኛ የሚመጡ ታካሚዎች በወቅቱ አስፈላጊውን እርዳታ የሚያገኙበት ምቹ ክፍሎችና መሳሪዎችም የተሟሉ ከመሆኑም በላይ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችንም ተጣቃሚ አድርጓል ነው ያለችው። ለረጅም ዓመታት በቲቢና በሳምባ ነቀርሳ በሽታዎች ህክምና ላይ ብቻ አትኩሮ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት አቅሙን በማሳደግ የአገልግሎት አድማሱን እያስፋፋ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ያእቆብ አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት የመመረዝ አደጋን ጨምሮ የልብ፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የህጻናትና የጨቅላ ህጻናት፣ የቆዳ፣ የህጻናት የስነ አእምሮ እና የድንገተኛ ህክምናዎችን ለህዝቡ በመስጠት ላይ ይገኛል። ማእከሉ ከድንገተኛ እስከ ጽኑ ህክምና ክፍሎችን ያደራጀ ሲሆን ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅምም ገንብቷል። ከመርዝና ከባእድ ነገር ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ የጤና ጉዳት ለሚዳረጉ፤ በተለይም ኩላሊታቸው መስራት ላቆመ ታካሚዎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎትም በማዕከሉ ይሰጣል ብለዋል ስራአስኪያጁ። ከመመረዝ ጋር በተያያዘ የጤና እክል የሚያጋጥማቸው ዜጎች ካሉበት ቦታ  ህክምናም ሆነ የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የመረጃ ማዕከል ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስኪያጁ ከኢቲዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር  ነጻ የስልክ መስመር ለመክፈትም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ህብረተሰቡ ከቀናት በኋላ ለአገልገሎት ክፍት በሚሆነው "8939" ነጻ የስልክ መስመር በመጠቀም አፋጣኝ እርዳታ መጠየቅ ይችላሉም ተብሏል። በተለይ በመሳሪያ የታገዘ ህክምና የማያስፈልጋቸው ታካሚዎች በነጻ የስልክ መስመሩ አማካኝነት ከህክምና ባለሙያ ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ የሚያግዛቸውን መረጃ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም