የደጃዝማች ባንጃው ቤተ-መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የደጃዝማች ባንጃው ቤተ-መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ
አሶሳ ሚያዚያ 21/2011በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ የሚገኘው የደጃዝማች መሐመድ ባንጃው ቤተ-መንግስት በደረሰበት ጉዳት እየፈራረሰ በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ።
የቤተ-መንግስቱ ጥገና እና የተዘረፉ ሀብቶችን ለማስመለስ የክልሉ መንግስት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
የጉባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ፋሪስ መሐመድ ሐምዳን በሰጡት አስተያየት ደጃዝማች መሐመድ ባንጃው ቅድመ አያታቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት ቤተመንግስቱ ከ27 ዓመት በፊት በመንግስት ለውጥ ወቅት በደረሰበት ዘረፋ ጣሪያው፣ በርና መስኮቱ ተነቃቅሎ ተወስዷል፡፡
"ቅርሱ የሀገሪቱን ታሪክ እና በወቅቱ የነበረውን የህንጻ ጥበብ ያሳያል" ያሉት አስተያየት ሰጪው ቅርሱን ከመጠበቅ አንጻር የድርሻቸውን እንደተወጡ ተናግረዋል፡፡
ቅርሱ የቤት እንስሳት መዋያ በመሆኑ ለከፋ ጉዳት መዳረጉን የገለጹት ነዋሪው የኢትዮጵያ ህዝብና ከወረዳ እስከ ፌዴራል የሚገኙ መንግስታዊ አካላት ለቅርሱ ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል።
ቤተመንግስቱን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደጎበኙ የሚናገሩት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጸሐይ ሞርካ ለቤተመንግስቱ ጥገና በተደጋጋሚ በፌደራል መንግስት ጨረታ መውጣቱን አስታውሰዋል።
በወጣው ጨረታ ጥገና የሚያደርግ አካል ማግኘት አለመቻሉን አመልክተዋል፡፡
ጥገናው ከፍተኛ በጀት እንደሚጠይቅ የገለጹት ኃላፊዋ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር ቅርሱ በሚታደስበት ሁኔታ ላይ እየተነጋገሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አድጎ አምሳያ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ ጥገና ለማድረግ ቢያቅድም ሳይሳካ እንደቀረ ተናግረዋል፡፡
በሚቀጥለው የበጀት ዓመት የቤተመንግስቱ ጥገና እና የተዘረፉ ሀብቶችን ለማስመለስ የክልሉ መንግስት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ቅርሱን ለመጠበቅ ያደረጉትን ጥበቃ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ከጉባ ወረዳ ማንኩሽ ከተማ በሁለት ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የሚገኘው የደጃዝማች መሐመድ ባንጃው ቤተ-መንግስት የተሰራው በ1934 ዓ.ም ነው።
የቤተ መንግስቱ አንዳንድ ክፍሎች ዲዛይን ከአጼ ፋሲል ግንብ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆን ከህዳሴው ግድብ ቀጥሎ የወረዳው ዋነኛ የቱሪስት መስህብ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ከሁለት ሄክታር በሚበልጥ ቦታ ላይ ያረፈው ቤተመንግስቱ የመኖሪያ፣ እንግዶች መቀበያ፣ የአናብስት ማደሪያ እና ሌሎችም ክፍሎችን አካቶ ዙሪያው ከሁለት ሜትር በሚበልጥ ከፍታ ባለው ግንብ የታጠረ መሆኑ ታውቋል፡፡