የፕሪሚየር ሊጉ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ
ሚያዝያ 21/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ፡፡
የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ዓ.ም መካሄድ የነበረባቸው ቢሆንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የመርሃ ግብር ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ ጨዋታዎቹ የሚደረጉበት ቀናት መቀየሩ የሚታወስ ነው።
በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት ቅዱስ ጊዮርጊስ የፕሪሚየር ሊጉን መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ የሚያስተናግድበት መርሃ ግብር የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሆኗል።
በ22ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በክልልም ከተሞች 7 ጨዋታዎች የሚካሄዱ ይሆናል።
በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ፣በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በጅማ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋር ከሲዳማ ቡና፣ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከደደቢት ይጫወታሉ።
በሶዶ ስታዲየም ደግሞ ወላይታ ድቻ ከመከላከያ፣ በሽሬ ስታዲየም ስሑል ሽረ ከሀዋሳ ከነማ እና በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ ከደቡብ ፖሊስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሁሉም የክልል ጨዋታዎች የሚካሄዱት በተመሳሳይ 9፡00 ነው።
የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ45 ነጥብ ሲመራ፣ ፋሲል ከነማና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 37 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
መከላከያ፣ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ይገኛሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በ13 ግቦች ሲመራ፣ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በ12 የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ11 ግቦች ይከተላል።