የትግራይና አፋር ክልላዊ መንግስታት በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይና አፋር ክልላዊ መንግስታት በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለፁ
ሚያዝያ 20/2011 የትግራይ ክልላዊ መንግስት በቀድሞ የኢትዮጵያ ፌዴራለዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ፕሬዚደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ።
የትግራይ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የክልሉን መንግስት የሀዘን መግለጫ ጠቅሶ እንዳስታወቀው በፕሬዚደንቱ ህልፈተ ህይወት ጥልቅ ሀዘኑን በመግለጽ ለቤተሰቦች፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።
በሌላ በኩል የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በቀድሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ፕሬዚደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈት ህይወት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ዶክተር ነጋሱ ጊዳዳ በህይወት ዘመናቸው መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ተቀብለው በማገልገል ለትውልድ አርአያነት ያለው ተግባር ፈጽመዋል።
በተለይም ከሙስና በጸዳ መልኩ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለህዝባቸውና ለሀገራቸው እድገት በማዋል ገንቢ ሚና መጫወታቸውንም አመልክቷል።
የአፋር ክልላዊ መንግስት በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሕልፈተ ህይወት የተሰማውን ልባዊ ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያዊያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።