የደቡብና የሐረሪ ክልላዊ መንግስታት በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብና የሐረሪ ክልላዊ መንግስታት በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
ሀዋሳ እና ሐረር ሚያዝያ 20/2011 ኢዜአ የደቡብ እና የሐረሪ ክልላዊ መንግስታት በቀድሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ።
የደቡብ ክልላዊ መንግስት ፕሬስ ሴክሬተርያት ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው የክልሉ መንግስት የሀዘን መግለጫ እንዳስታወቀው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከ1987 እስከ 1993 ዓ.ም በፕሬዚዳንትነት ባገለገሉባቸው ሰባት ዓመታት በርካታ በጎ ተግባራትን አከናውነዋል።
የኢፌድሪ ህገመንግስትን ከማርቀቅ አንስቶ በተለያዩ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ዙሪያ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጸው የክልሉ መንግስት በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል።
በተመሳሳይ የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት በቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ፕሬዚዳንት በመሆን ከማገልገላቸውም በላይ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዘረጋ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው የሐረሪ ክልላዊ መንግስት መግለጫ አስታውሷል።
በዚህ ታላቅ ሰው ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦች ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው ኢትዮጵያዊያን መፅናናትን ተመኝቷል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም እንዲሁ ሀዘኑን ገልጿል
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በጀርመን ሀገር ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ሚያዚያ 19/2011 ዓ.ም ነው ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ነው የተሰማው።