ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ

ሚያዝያ 19/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ

በጀርመን ባለፉት ሶስት ሳምንታት በህምክና ሲረዱ የቆዩት የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት  ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ዛሬ ተሰምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዜና እረፍት የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መግለጻቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የቀብር ሥነ ሥርዓትን በተመለከተ ብሔራዊ ኮሚቴ እንደሚቋቋምና ዝርዝር ጉዳዮችን በየጊዜዉ የሚገለጹ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ነሐሴ ወር መጨረሻ በ1935 ዓ.ም በምዕራብ ኢትዮጵያ ደምቢዶሎ የተወለዱት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ላለፉት 30   ዓመታት ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው።

ከ1987 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።

ዶክተር ነጋሶ በማህበራዊ ታሪክ ከፍራንክፈርት አም-ሜይን ጎተ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።

ጀርመናዊቷን ነርስ ሬጂና አቤልት አግብተው በትዳር ኖረዋል።

ዶክተር ነጋሶ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሾማቸው በፊት የሽግግር መንግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ (ኢህአዴግ) ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞው የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ነበሩ።

ዶክተር ነጋሶ የስልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ ወራት ሲቀራቸው ከኦህዴድና ከኢህአዴግ ጋር ባለመግባባት ለቀው መውጣታቸው ይታወቃል።

በ1997 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ በግል ተወዳዳሪነት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ደምቢዶሎ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው በማሸነፍ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመግባት የህዝብ እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል።

በሐምሌ 2000 ዓ.ም የዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሲመሰረት መስራች አባል በመሆን በፓርቲው ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም