ቀጥታ፡

የበጎ አድራጎት ስራዎች በበአላት ብቻ ሊወሰኑ እንደማይገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ

ሚያዚያ 19/2011 የበጎ አድራጎት ስራዎች በበአላት ብቻ ሳይወሰኑ የሰውን ህይወት ወደ ሚቀይር ተግባር ሊውሉ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ ::

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የምሳካየ ሃዙናን መድሃኒአለም ገዳም የሃይማኖት መምህሩ አባ ገብረእየሱስ ቢልልኝ እንደተናገሩት ከምእመናን ጋር በመሆን የገዳሙ ሶስት አባቶች በፋሲካ እና በገና በአል ከአራት እስከ አምስት ሺህ ነድያንን ያበሉ እንደነበር ያስታውሳሉ ፡፡

ነገር ግን ይህ ተግባር ብቻውን የሰዎችን ህይወት ሊቀይር እንደማይቻል በመገንዘብ  ለችግረኛ ተማሪዎችና ለደካማ እናቶች ወርሃዊ እርዳታ ወደ ማድረግ መሸጋገሩን ያወሳሉ፡፡

“ተማሪዎች በቂ ምግብ ባለማግኘት በትምህርት ቤትያንቀላፋሉ” ያሉት የሃይማኖት አባት እናቶችም ሲወጡ ሲወርዱ ኖረው ያለጧሪ የሚቸገሩበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ምእመናን በማስተባበር ለ20 ተማሪዎች የአመት የደንብ ልብስና  ወርሃዊ እርዳታ 400 ብር በማድረግ አድገውም ለሃገር ሸክም እንዳይሆኑ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ለ 15 እናቶች እራሳቸውን ለማስቻል ከራስ አገዝ  ድርጅት ጋር በመተባበር ስልጠና አግኝተውና ብድር ወስደው እየሰሩ እንዲቆጥቡ መደረጉንም ይናገራሉ፡፡ 

“የኢትዮጵያ ህዝብ በየትኛውም ሃይማኖት የመስጠትና የመመፅወት ልምድ አለው ”የሚሉት የሃይማኖት አባቱ ይህንን በጎ ምግባር የሰዎችን ህይወት ወደ ሚቀይር ተግባር ማዋል ግን “ይቀረናል” ብለዋል፡፡

ምፅዋት መስጠትንም ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ስራን ባህሉ አድርጎ መቆጠብንም እንዲለማመድ መስራት እንደሚገባም ነው የገለፁት ፡፡

በመንግስት በኩልም ለስራ ፈጣሪዎች ቦታና ገበያውን የማስተሳሰር ተግባርን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በእንጦጦ መካነእየሱስ ማህበረ ምእመናን መሪ ካህን ቄስ ጀምስ  ጎበና በበኩላቸው እየሱስ ክርስቶስ በጎነትን ያደረገው   ምሳሌ ለመሆን ነው ፤በጎ መስራትም የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት ነው ይላሉ፡፡

በቤተክርስቲያኗ በአልን አስታኮ የሚከናወኑ በጎ ስራዎች እንዳሉ ሁሉ ከምእመናን መዋጮ ለችግረኛ ተማሪዎች  የደንብ ልብስና  ቦርሳ እንዲሁም የቤት ኪራይ የሚከፈልበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል ፡፡

ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን እናትም አባትም  ሆኖ ለማሳደግ በሃገር ውስጥ የሚደረገው በጎ ምግባር የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በአላትንም በችግር ውስጥ ካሉ ህፃናት ጋር ማሳለፍ እንደሚገባ ነው የገለፁት ፡፡

“አብሮ መኖርና መካፈል ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ ነገር አይደለም” ያሉት የሃይማኖት አባት አንድነት ፣ፍቅር ላጣው መስጠት፣ የታመመ መርዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት ፡፡

“ያጣነውን አንድነት ልንመልሰው ይገባል” ያሉት የሃይማኖት አባቱ ኢትዮጵያዊነት መልካምነት በመሆኑ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ የመኖርና የመስራት መብቱ ተከብሮለት ሊኖርና ለሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም