ቀጥታ፡

የትንሳኤ በዓል ሲከበር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው የአብሮነት፣የመተሳሰብና የመቻቻል ባህልን በማዳበር ሊሆን ይገባል-የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ ሚያዝያ 19/2011 የትንሳኤ በዓል ሲከበር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የመቻቻል ባህልን በማዳበር ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

በዓሉ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ግዴታን ባለመርሳት፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን በማገዝ፣ ለችግረኞች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለተራቡና ለተጠሙ ወገኖች ካለን ላይ በማካፈል መሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ ለህዝበ - ክርስቲያኑ ለትንሳኤ በዓል የ"እንኳን አደረሳችሁ" መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

አባ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት ቃለ ቡራኬ ህዝበ ክርስቲያኑ ለአገር አንድነት፣የዜጎችን ክብርና ደኅንነት በመጠበቅ የኢትዮጵያዊነት ባህልና ሃይማኖታዊ ስረዓትን በማዳበር ሊከበር ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም ''ለዘላቂ ልማትና እድገት፣ለፍጹም ወንድማዊ ፍቅርና ስምምነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ አጥብቀን መስራት አለብን'' ሲሉም አሳስበዋል።

የአገሪቷን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች የሆኑትን የሰላም የአንድነትና ከድህነት የመላቀቅ ጥያቄዎች በአስተማማኝ ሁኔታ የሚመለሱት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ጭፍን ጥላቻ፣ ራስ ወዳድነት፣ ለእኔ ብቻ ይድላኝ ባይነትን ፣በጥርጣሬ ዓይን መተያየትን፣ አለመተማመንን መጨካከንን፣ መለያየትና አንዱ ለሌላው ስጋት መሆንን ማስወገድ ሲቻል ነውም ብለዋል።

በዚህም በፍቅር፣ በወንድማማችነት፣ በኅብረት፣ በስምምነት፣ በአንድነት፣ በመከባበር በመተማመን፣ በይቅር ባይነት በመደጋገፍና በመተዛዘን መንፈስ ሁላችንም አጥብቀን ከሰራን በሁሉም ዘርፍ አሸናፊ መሆን ይቻላል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ በበኩላቸው የተሰጠንን የህይወት ጊዜ በፍቅር፣ በይቅርታና በመቻቻል ኑሮ የኢትዮጵያን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

የሰላምና የመግባባት መንፈስ በመላው የአገሪቷ ዜጎች ውስጥ መኖር እንደሚገባውም ጠቅሰዋል ካርዲናል ብርሃነየሱስ።

ምዕመናኑ በዓሉን ልክ እንደ ቀደምቶቹ ክርስቲያኖች አንድ በመሆንና በአገራችን የተለያዩ ቦታዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች በመርዳት ማሳለፍ እንደሚገባም ነው የገለፁት።

የትንሳኤ በዓል ሲከበር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው የአብሮነት፣የመተሳሰብና የመቻቻል ባህልን በማዳበር ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ ናቸው ።

"በዓሉ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ፍቅሩንና መስዋዕትነቱን ያሳየበት ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ የክርስትና እምነት ተከታዮችም ይህንን የአምላካቸውን አርአያነት መከተልና ማስረጽ ይገባናል ብለዋል።

በአገሪቷ አሁን አሁን ፈጽሞ ከኢትዮጵያዊነት ባህልና ሃይማኖት ባፈነገጠ መልኩ ዜጎች ለግጭትና ላለመግባባት እየተዳረጉና አብሮ የመኖር ባህላቸው እየተሸረሸረ ይገኛልም ብለዋል።

በዚህ በእርስ በእርስ ግጭቶችና አለመግባባቶች ሳቢያም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ በመሆኑ በዓሉ እነሱንና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ሊከበር እንደሚገባ አክለዋል።

በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶች የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በዜጎች መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን በመነጋገር እንዲፈቱና ወደ ቀድሞ ኢትዮጵያዊ ባህል እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም የሃይማኖት አባቶቹ መልእክታቸወን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም