በመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ሻምፒዮና ቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ

106

ነቀምቴ ሚያዝያ18 /2011 በነቀምቴ ስታድየም ከሚያዝያ 6 እስከ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲካሄድ የቆየው   የመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ሻምፒዮና በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

በ20 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሮች በተካሄዱበት ሻምፒዮና ላይ 4ሺህ 363 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል ።

በሻምፒዮና ውድድሩ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር  ሰባት ዋንጫዎችን በማግኘት አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።

የነቀምቴ ከተማ አምስትና የሻሸመኔ ከተማ አራት ዋንጫዎችን በማግኘት ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል ።

የኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ናስር ሁሴን ሻምፒዮና ውድድሩ የአካባቢው ስፖርትና የንግድ እንቅሰቃሴ እንዲነቃቃ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል ።

"ሻምፒዮናው ስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት በመሆኑ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቋል" ብለዋል።

ሻምፒዮና ውድድሩ ክልሉን ወክለው በኢትዮጵያ ደረጃ የሚሳተፉ ጠንካራና አቅም ያላቸው ስፖርተኞችን ለመመልመል የሚያግዝ ነው።

በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው እንደተናገሩት የወለጋ ስታዲየም መገንባቱ የመላው ኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴን ለማሳደግ አስተዋጽኦ  አለው።

ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያበረክተው አስተዋዕኦም የጎላ መሆኑን ገልፀዋል ።

"ስፖርት ፍቅርና መተሳሰብን የሚያዳብር በመሆኑ ዘርፉን ለማሳደግ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል "ብለዋል ።

የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ ቦጋለ ሹማ  ስፖርተኞችና የስፖርት ቤተሰቦች በጨወታው ወቅት ያሳዩት አንድነት፣ፍቅርና መቻቻል ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም በኃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም