በ25ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መከላከያ ፋሲል ከተማን 1ለ0 አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በ25ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መከላከያ ፋሲል ከተማን 1ለ0 አሸነፈ
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዛሬ በአጼ ፋሲለደስ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ መከላከያ ፋሲል ከተማን 1ለ0 በሆነ ውጤት አሸነፈ። በጎንደር ባለው ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ምክንያት ፋሲል ከተማ ከመከላከያ ዛሬ ረፋዱ አራት ሰአት ላይ ጨዋታቸውን እንዲያካሂዱ መደረጉ ይታወቃል። ምንይሉ ወንድሙ 80ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ማሸነፍ የቻለው መከላከያ ነጥቡን ወደ 32 ከፍ በማድረግ ከነበረበት 11ኛ ደረጃ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ያለ ሲሆን 34 ነጥብ ያለው ፋሲል ከተማ በነበረበት ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቀሪ የ25ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ዛሬ የሚካሄዱ ሲሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ወልድያ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በሃዋሳ ስታዲየም ሃዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና እና በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ይጫወታሉ። በድሬዳዋ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በሚደረገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ የፕሪሚየር ሊጉን መሪ መቐለ ከተማን ያስተናግዳል። በ25ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች መካከል በጅማ ስታዲየም ጅማ አባጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። የደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት ተከትሎ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢት ከአርባ ምንጭ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ከተማ በ42 ነጥብ ሲመራ፣ ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 41 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ናይጄሪያዊ ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ15 ጎሎች ሲመራ፣ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በ11 የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በ10 ግቦች ይከተላሉ።