የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለ72 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

135

ቤኒሻንጉል ሚያዝያ 17/2011የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለ72 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን ገለጸ፡፡

በክልሉ የይቅርታ ዓዋጅ መሠረት ይቅርታ ቦርድ በየሩብ ዓመቱ የይቅርታ መስፈርቱን ለሚያሟሉ  ታራሚዎች ይቅርታ እንዲሰጥ ይደነግጋል፡፡

ታራሚዎች ይቅርታ የተደረገላቸው ዓዋጁ  መሠረት በማድረግ መሆኑን የክልሉ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ  ዮሐንስ ተሰማ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ከአሶሳ 40፣ ከመተከል 30 እንዲሁም ሁለት በካማሽ ማረሚያ ቤቶች በእርምት ላይ የቆዩ ናቸው።

ይቅርታ ከተደረገላቸው መካከላቸው አራቱ ሴቶች መሆናቸውንም አስታውቀዋል ፡፡

ይቅርታውን ያገኙት ታራሚዎች በፍርድ ቤት ከተወሰነባቸው የእስር ጊዜ አንደ ሶስተኛውን የጨረሱ ሲሆን፣  ከኅብረተሰቡ ቢቀላቀሉ ምርታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቦርዱ ማጣራቱን አስረድተዋል፡፡

የቦርዱ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በማረሚያ ቤቶቹ በአካል ተገኝተው የታራሚዎችን መዝገብና ተያያዥ ጉዳዮችን  በጥንቃቄ መርምረዋል ብለዋል፡፡

ምክትል ዐቃቤ ሕጉ እንደሚሉት ይቅርታው አስገድዶ መድፈር፣ ጠለፋ፣ ያለእድሜ ጋብቻ፣ ሙስና፣ ከባድ ግድያ እና ዘረፋ፣ የህጻናትና ሴቶችን ጉልበት ብዝበዛ፣ ሃሰተኛ ሰነድና ሌሎችንም አስከፊ ወንጀሎች ፈጽመው በህግ ጥላ ሥር  የሚገኙትን አይመለከትም፡፡

ይሁንና እነኚህን ወንጀሎች ፈጽመው ኤች አይቪኤድስ፣ ካንሰር፣ ስኳርና ሌሎችንም የማይድኑ ሕሙማን መሆናቸው በትክክለኛ የሃኪም ማስረጃ ሲረጋገጥ ይቅርታ እንደሚያገኙ አቶ ዮሐንስ አብራርተዋል፡፡

በክልሉ በዚህ በጀት ዓመት የዛሬዎችን ታራሚዎች ጨምሮ 163 ሰዎች የይቅርታ አዋጁ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም