ኬንያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች የተመሰረተው ማህበር ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጁ ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
ኬንያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች የተመሰረተው ማህበር ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጁ ሆኗል
አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊነት ኬንያ በነበሩበት ወቅት በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሙያተኞች ተሰባስበው ያቋቋሙት ማህበር ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅቱን መጨረሱን ነው አባላቱ የሚናገሩት።
ማህበሩ የተመሰረተው በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኬንያ የስራ ጉብኝት አድርገው በተመለሱ ማግስት ነው።
የማህበሩ አባል የሆኑትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ በአፍሪካ ቢሮ የኢነርጂ ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር መሰረት ተክለማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የማህበሩ አባላት ባላቸው ሙያ ኢትዮጵያን ለማገልገል ዝግጁ ናቸው።
ይህንን ዝግጁነታቸውን ለመንግስት አሳውቀው መንግስትም በሙያቸው ማገልገል እንደሚችሉ አረጋግጦላቸዋል።
በጀርመን የልማት ትብብር (ጂ አይ ዜድ) ውስጥ አማካሪ የሆኑት ሌላዋ የማህበሩ አባል ወይዘሪት አስቴር በቀለም ማህበሩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና ፋይናንስ በማፈላለግ ስራዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ይሰራል።
የማህበሩ አባላት በሙያቸው ለማገልገል ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸው፤ የሙያተኞቹ ቅንጅት ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
በተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ የዱር እንስሳትና ደን ባለሙያ የሆኑት የማህበሩ አባል ዶክተር ታዬ ተፈሪ በበኩላቸው ማህበሩ የጤና ፣ የፋይናንስ፣ የዕቅድ፣ የትምህርት፣ የአካባቢ ጥበቃ የሌሎች ሙያዎች ባለቤት የሆኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዳሉት ተናግረዋል።
የማህበሩን አባላት እንደሙያቸው በማደራጀት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሚኒስቴሮችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀራረብ ለመስራት እየተሞከረ እንደሆነም ገልጸዋል።
ኬንያ በሚገኙ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከፍተኛ ክህሎት እንዳላቸው የገለጹት በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም፤ ባለሙያዎቹ ለአገራቸው አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ የማስተሳሰር ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ባለሙያዎቹ ድጋፍ ተደርጎላቸው በሙያቸው ኢትዮጵያን እንዲያገለግሉ ማመቻቸት ከተቻለ ብዙ መጠቀም እንደሚቻልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የማህበሩ አባላት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለኢትዮጵያ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የናይሮቢ ምዕራፍን ለማጠናከር ንቁ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ አባላቱ የአንድ ዓመት መዋጮ ከወዲሁ እንዲከፍሉ አድርገዋል።