በአማራ ክልል ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችና ንብረት ሲያጓጉዙ የተደረሰባቸው 692 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል

74

ሚያዝያ  17/2011 በአማራ ክልል ባለፉት ወራት ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችና ንብረት ሲያጓጉዙ የተደረሰባቸው 692 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ገብሩ ታመነ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተመረጡ በሮች በተካሄደ ጥበቃ ነው፡፡

ከህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹም 671 የተለያዩ መሳሪያዎች፣ ከ5 ሺህ በላይ የቁም ከብቶች፣ 578 ሽጉጦችና ከ16 ሺህ 200 የሚበልጡ ጥይቶች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

ንብረቶቹ የተያዙትም በመውጫና መግቢያ በሮች እንዲሁም በመሠረተ ልማትና ድልድዮች በተካሄደ ጥበቃና ስምሪት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ንብረት ከተያዙባቸው አካባቢዎችም በምዕራብ ጎንደር መተማ፣ ቋራ፣ አርማጭሆ፣ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ጃዊ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬና ሰሜን ወሎ ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉት ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን አቶ ገብሩ አስረድተዋል።

የቁም እንስሳቱ ባለቤቶቻቸው ተለይተው እንዲመለሱ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በየአካባቢው በሚሊሻ አባላት፣ ከአካባቢው ማህበረሰብና የፀጥታ መዋቅሩ ጋር ትብብር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር እያደረገ ያለውን ትብብር እንዲያጠናክር ያሳሰቡት  የቡድን መሪው፣ አጠራጣሪ ጉዳይ ሲገጥምም በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ መዋቅር እንዲጠቆም አሳስበዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው ዓመትም በህገ ወጥ እንቅስቃሴ የተሳተፉ ከ1 ሺህ 200 በላይ ህገ ወጦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም