በዝግ ስታዲየም የተካሄደው የወላይታ ድቻና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ 0ለ0 ተጠናቀቀ

142

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011 በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ረብሻ እንዳይካሄድ የተደረገው የወላይታ ድቻና የደቡብ ፖሊስ 21ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በዝግ ስታዲየም በአዲስ አበባ ተካሂዶ 0ለ0 ተጠናቀቀ።

ባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመካሄዱ በፊት በደጋፊዎች በተነሳ ረብሻ ሳይካሄድ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም በዝግ እንዲካሄድ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ዛሬ ተካሂዶ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

በተመሳሳይ ሚያዚያ 13 ቀን 2011 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት የሃዋሳ ከተማና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድኖች ጨዋታ በጸጥታ ስጋት የተነሳ ሳይካሄድ ቀርቷል።

ፌዴሬሽኑ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ሃዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ እንዲጫወት በመወሰኑ ዛሬ በአሰላ ስታዲየም ጨዋታው ተካሂዷል።

በጨዋታው ያለምንም ግብ 0ለ0 በሆነ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም