በሳምንቱ ከአንድ ሺህ በላይ ስደተኞችን ወደ አገር ቤት መልሻለሁ-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

47

ሚያዝያ 17/2011 በተያዘው ሳምንት በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገር ቤት መመለሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው እንዳሉት ፤ ስደተኞቹ የተመለሱት ከታንዛንያ፣ የመንና ሳዑዲ ዓረቢያ  ነው።

በሳምንቱ ኦኮንጓ፣ ሴጌራና ሞሮጎሩ በሚባሉ ግዙፍ የታንዛኒያ እስር ቤቶች የነበሩ 288 ኢትዮጵያውያንን በማስፈታት ወደ አገራቸው መመለስ ተችሏል ሲሉም ነው ያብራሩት።

እስረኞቹን ለማስፈታት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የታንዛኒያ የስራ ኃላፊዎች ጋር ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።

እስረኞቹን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚያስፈልገውን የትራንስፖርትና ታያያዥ ወጪ ደግሞ ከዓለም የስደተኞች ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤት ጋር በመተባባር መሸፈኑን አውስተዋል።

የተጠቀሱትን እስረኞች ሳይጨምር መንግስት ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከታንዛኒያ እስር ቤቶች ስድስት መቶ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን አስፈትቶ ወደ አገራቸው መመለሱንም አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በየመን በአስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ 13 ስደተኞችን ከአንድ ቀን በፊት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን ነው ገለጹት።

በተመሳሳይ በሳዑዲ ዓረቢያ ያለመኖሪያ ፈቃድ ይኖሩ የነበሩ 850 ኢትዮጵያውያንን በራሰቸው ፈቃድ ወደ አገራቸው የመመለስ ስራ መከናወኑን አቶ ነብያት አብራርተዋል።

ጅዳ የሚገኘው የኢፌዴሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባባር ስደተኞቹን ከሳዑዲ ዓረቢያ የማስመለሱ ስራ እውን እንዲሆን ማድረጉንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም