የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ለ11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከአልጄሪያ አቻው ጋር ነገ ይጫወታል

115
አዲስ አበባ ግንቦት 28/2010 የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ኅዳር ወር 2011 ዓ.ም በጋና በሚካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻውን ማጣሪያ ጨዋታ ነገ አልጀርስ ላይ ከአልጄሪያ አቻው ጋር ያደርጋል። ሉሲዎቹ  ከሊብያ ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታ  በደርሶ መልስ 15 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል። በአፍሪካ ዋንጫው ለመሳተፍ የአልጄርያን ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። የመልሱ ጨዋታ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል። የማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ግንቦት 25 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አልጄሪያ ያቀናው ብሔራዊ ቡድኑ ለጨዋታው ቅድመ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ለአንድ ወር በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርግ ቆይቷል። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚሰለጥኑት ሉሲዎቹ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ ክለቦች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገዋል። ብሔራዊ ቡድኑ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ ለአራተኛ ጊዜ በአፍሪካ የሴቶች የእግር ኳስ ዋንጫ መሳተፉን ያረጋግጣል። የቡድኑ አባል ሎዛ አበራ በአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራች ሲሆን የቡድን አጋሯ የፊት መስመር ተጫዋቿ ረሂማ ዘርጋው በአራት ግቦች ትከተላታለች። እኤአ በ2002 ሉሲዎቹ በ5ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ተሳትፎ ከምድባቸው ያላለፉ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ 6ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ በማሊ ተሸንፈው አራተኛ ደረጃን በመያዝ ያስመዘገቡት ውጤት በታሪክ ከፍተኛው ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም