በወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያን ወክለው ለተወዳደሩ ስፖርተኞች እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያን ወክለው ለተወዳደሩ ስፖርተኞች እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2011ኢትዮጵያን በመወከል በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ወርልድ ቴኳንዶ ለተወዳደሩ ስፖርተኞች እውቅና የመስጠት ፕሮግራም በአዲስ አበባ ተካሄደ።
በአህጉር አቀፍና እና ዓለም አቀፍ ወርልድ ቴኳንዶ ውድድሮች ባለፈው አንድ ዓመት ኢትዮጵያን ወክለው ውጤት ላስመዘገቡ ስፖርተኞች እውቅና የመስጠት ፕሮግራም ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ሆቴል ተካሄዷል።
ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 2011 ዓ.ም በተካሄዱት ውድድሮች ኢትዮጵያ 5 የወርቅ 2 የብርና 3 የነሐስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ሜዳሊያዎቹ የተገኙት በሞሮኮ፣ቱርክ፣አልጄሪያና ፖላንድ በተካሄዱ ውድድሮች ነው።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ወርልድ ቴኳንዶ ከአትሌቲክሱ በመቀጠል በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለኢትዮጵያ ውጤት እያስገኘ ያለ ስፖርት ነው።
ኢትዮጵያን ወክለው ውጤት ያስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች በመንግስት በኩል እውቅና ተሰጥቷቸው ማበረታቻ እየተደረገላቸው ባለመሆኑ ተወዳዳሪዎች እና አሰልጣኞች ሞራል እየጎዳ እንደሆነም ተናግረዋል።
የእውቅና ፕሮግራሙም የተዘጋጀው ውጤት ላመጡት ተወዳዳሪዎች ምስጋና ለማቅረብና ለማበረታት እንደሆነና መንግስትም አገርን ወክለው ለሚወዳደሩ ስፖርተኞች ተገቢውን ማበረታቻ ማድረግ እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በዓመቱ ከተገኙት አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎች ሶስቱን ያገኘው ሰለሞን ቱፋ መንግስት ለእግር ኳስና አትሌቲክስ እንደሚሰጠው ትኩረት ለወርልድ ቴኳንዶ እየሰጠ እንዳልሆነ ገልጿል።
የወርልድ ቴኳንዶ ክለቦች እንዲቋቋሙ፣ተወዳዳሪዎች በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲሳተፉ አስፈላጊውን የፋይናንስ ወጪ ከመሸፈን አኳያና ስፖርቱ እንዲያድግ መንግስት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ አይደለም ብሏል።
በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት እየተገኘ ያለው ውጤት ዘላቂነት እንዲኖረው መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብሏል።
የወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣዩ ዓመት በጃፓን በሚካሄደው የቶኪዮ አሎምፒክ ውድድር ውጤት ለማስመዝገብ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግሯል።
ሌላኛዋ የወርልድ ቴኳንዶ ተወዳዳሪ ናርዶስ ሲሳይ የመገናኛ ብዙሃን ስፖርቱን ህዝቡ እንዲያውቀው ከማድረግ አንጻር የሰሩት ስራ በቂ አለመሆኑን አንስታለች።
የመገናኛ ብዙሃን ስፖርቶች አንዲያድግና በህዝቡ ዘንድ እውቅና እንዲኖረው በማድርግ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ገልጻለች።
የወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማስተር አዲሱ ኡርጌሳ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍና በአህጉር አቀፍ መድረኮች እያስጠራ ያለው የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ተገቢውን እውቅና እንዳላገኘ ጠቅሷል።
መንግስት እንደ ሌሎች ስፖርቶች ወርልድ ቴኳንዶን በእኩል አይን ማየት ቢጀምር ሲልም መልእክቱን አስተላልፏል።
የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ባልቻ ለስፖርተኞች ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደረግ ገልጸው የሚሰጠው ሽልማትም ውጤት ላይ መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ከለያቸው ስፖርት ፌዴሬሽኖች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን መሆኑንም አስረድተዋል።
በውድድሮች ተሳትፎ ለነበራቸው ፖርተኞች የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው በግላቸው ለእያንዳንዳቸው ተወዳዳሪዎች የ10 ሺህ ብር ሽልማት አበርክተዋል።
የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት ለወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን አባላት የስፖርት ትጥቅ ገዝተው ለማበርከትም ቃል ገብተዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደተገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኮሪያዊያን የባህል ስፖርት በሚል የሚታወቀው ወርልድ ቴኳንዶ ከሰውነት ፍልሚያ ባሻገር ጥበባዊ ስልቶችን ያካተተ ክንዋኔ ሲሆን አዕምሮና ሰውነት ማሰልጠንን ጨምሮ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት የሚያግዝ የስፖርት ዓይነት እንደሆነም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በ1995 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን ስፖርቱ ከአትሌቲክስ በመቀጠል በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ ውጤት በማስገኘት አገሪቷን በማስጠራት ላይ ይገኛል።