በባሌ ሮቤ ለሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

69
ሚያዝያ 16/2011 ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቲስ በተገኘ ድጋፍ ከ150 ሚሊዮን ብር ወጪ በባሌ ሮቤ ከተማ ለሚገነቡት አምስት የልማት ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቲስ በተገኘ ድጋፍ ከ150 ሚሊዮን ብር ወጪ በባሌ ሮቤ ከተማ ለሚገነቡት አምስት የልማት ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን በመወከል የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ረሺድ ሙሀባ ናቸው። ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ኮሚሽነሩ የክልሉ መንግስት ህዝቡ የሚያነሳውን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደእርሳቸው ገለጻ በተገኘው ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለመገንባት የታቀዱት የልማት ፕሮጀክቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንድ ማሳያ ናቸው ፡፡ መንግስት ተረጋግቶ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ሁለንተናዊ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ መስጠት እንዲችል የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን በመጠበቅ ፊቱን ወደ  ልማት እንዲያዞርም አቶ ረሺድ ጠይቀዋል፡፡ የዩናይትድ አረብ ኤሜሬት የልማት ፕሮጀክቶች ተወካይ ሚስተር ሰኢድ አል ኬሜሪ በበኩላቸው "የልማት ፕሮጀክቶቹ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር የሁለቱን ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር በኩል ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል" ብለዋል፡፡ የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ዲዲ በበኩላቸው እንዳሉት ከፕሮጀክቶቹ መካከል በሮቤ ሆስፒታል ውስጥ የሚገነባው የእናቶችና ህፃናት የህክምና ማዕከል ጨምሮ አራት የተለያየ ደረጃ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡ " በተለይ በሆስፒታሉ ውስጥ ለመገንባት የታሰበው የእናቶችና ህፃናት የህክምና ማዕከል የእናቶችና ህፃነት ህክምናን በተሻላ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጽኦው የጎለ ነው" ብለዋል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ተገንብተው ወደሥራ ሲገቡ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም እንዳላቸው የገለጹት ከንቲባው የመማሪያ ክፍሎች፣ የቤተ መጻህፍት፣ የላቦራቶሪና የአይሲቲና ሌሎች ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አጋዥ የሆኑ ተጨማሪ ክፍሎች እንዳሏቸው ተናግረዋል፡፡ የልማት ፕሮጀክቶቹ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት እንደሚበቁ የተገለጸ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በሚፈለገው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ማህበረሰቡ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ከከተማዋ ነዋሪዎቹ መካከል ሼህ ቃሲም ሁሴን በሰጡት አስተያየት በድጋፍ ለሚከናወኑት የልማት ፕሮጀክቶች ምስጋናቸውን አቅርበው "ለውጤታማነት የሚጠበቅብንን እንወጣለን" ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ መንግስት የገባውን ቃል ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ያሰየበት አጋጣሚ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ረታ በዳዳ ናቸው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም