የተፈጥሮ ጋዝን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ድርድር መጀመሩን የማዕድንና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ጋዝን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ድርድር መጀመሩን የማዕድንና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ገለጸ
ሚያዝያ 16/2011 በኢትዮጵያ በካሉብና ሂላላ የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ድርድር መጀመሩን የማዕድንና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ''ከመጋቢት እስከ መጋቢት በሚል'' መሪ ሀሳብ የተሰሩ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። ሚኒስቴሩ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ ግብ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል። ውጥኑ ይሳካ ዘንድም በመስኩ አቅም፣ ልምድና ካፒታሉ ለላቸው ኩባንያዎች ፍቅድ እየሰጠ ነው። የቻይናው ፖሊ ሲጂ ኤን ኩባንያ በካሉብና ሂላላ የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩን ማረጋገጡን ተከትሎ ምርቱን ለመሸጥ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ለዚህ የሚሆን ነዳጅ ማስተላለፊያ 760 ኪሎ ሜትር ቱቦለመዘርጋትም ከጅቡቲ ጋር ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል። ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንደገለጹት፤በኩባንያው የተገኘውን 4 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ኪዊቢክ ፊት ነዳጅ ወደ ገበያ ለማቅረብ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው። ''ምርቱን ለመሸጥም በርካታ ስምምነቶች መፈረም ይኖርባቸዋል'' ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ጅቡቲ የጋዝ ቱቦ ዝርጋታና የሚያስፈልጉ ፋሲሊቲዎች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል። በተመሳሳይም በአገራቱ መካከል ጋዙን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የንግድ ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል። ጋዙን ወደ ፈሳሽነት መቀየር የሚያስችል ግንባታም በጅቡቲ ወደብ ላይ እንደሚገነባ የተናገሩት ዶክተር ሳሙኤል የተፈጥሮ ጋዙን ወደ ገበያ ለማቅረብ አስፈላጊ መሰረተ ልማትና የስምምነት ውል ስራዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ በትንሹ ሁለት ዓመት ሊፈጅ እንደሚችልም ይጠቁማሉ። በሱማሌ ክልል በአንድ ኩባንያ 1 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ኪዪቢክ ፊት ነዳጅ የተገኘ መሆኑን ገልጸው ይህንንም ለማልማትና ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል። የነዳጅ ፍለጋውን ለማካሄድም በርከት ያሉ ኩባንያዎች ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል በትንሹ ስድስት ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ተፋሰሶች በአገር ደረጃ አሉ፤ ያልተያዙ ቦታዎች በኩባንያዎች እየተያዙ የምርመራ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ከነዳጅ ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግም ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ የነዳጅ ስራ ፖሊሲ በአዲስ መልክ ተከልሶ ስራ ላይ ለማዋል እንቅሰቃሴ እየተደረገ እንደሆነም አብራርተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኮያንግ ቱትላምማ በበኩላቸው ከካሉብና ሂላላ የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለዓለም ገባያ ማቅረብ የሚያስችል የንግድ ድርድር እየተደረገ ነው ይላሉ። ጋዙ እንዴት ቢሸጥ ያዋጣል? እንዲሁም እንዴት ይሸጣል? የሚለውን በአማካሪ ጥናት ተደርጎ በኩባንያውና በሚኒስትሩ መካል ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲልም ገልጸዋል። በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት አገሪቷ ከዘርፉ ጥቅም የምታገኝበት አሰራር እየተዘረጋ እንደሆነም አመልክተዋል።