ቀጥታ፡

የፈጠራ ጥበብ ዘርፍ ላይ የግል ባለሃብቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 16/8/2011 የፈጠራ ጥበብ ዘርፍ ላይ የግል ባለሃብቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑን የባህልና ቱረዝም ሚኒስቴር አስታወቀ:: ሚኒስቴሩ ዛሬ "የኪነጥበብ ዘርፍ ማነቆዎችና የባለሃብቱ ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከባለሃብቱና ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል:: ለውይይቱ የመነሻ ጽሁ ፍ   ያቀረቡት  የባህልና ቱሬዝም ሚኒስቴር የባህልና ኢንዱስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጽጌ  የፈጠራ ጥበብ ዘርፉ አጠቃላይ አበርክቶዎች ችግሮችና መፍትሄዎች የሚሏቸውን አብራርተዋል። የኪነጥበብ ዘርፉ በርካታ ችግሮች ውስጥ መሆኑን የገለጹት ዳይረክተሩ፤  ለዘርፉ የሚሆኑ ግብአቶች አለመሟላታቸው ትልቁ ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል። በዚህም ተቋሙ ከባለሃብቶች ጋር ተቀራርቦ የመስራት ውስንነት እንዳለበትም በማውሳት። የውይይቱ ተሳታፊና የሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ማናጀር አቶ ቢንያም አርጋው በበኩላቸው ኪነጥበብ በርካታ እሴቶችን ልናስተዋውቅበት የምንችለው የመገናኛ ዘርፍ በመሆኑ ባህልና እሴትን ሊገነቡና የአገርን ገጽታ ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ስራዎች ሲመጡ በደስታ ተቀብለው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። አቶ ቢንያም አያይዘውም እየመጡ ያሉ ስራዎች ግን እነዚህን የሚገልጹ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ፣ ባህልንና እሴትን የሚያዳብሩ ስራዎችን ለማገዝ ግን በራቸው ክፍት መሆኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ትያትር ባለሙያዎች ማህበር ምክተል ፕሬዝዳንት አቶ ቢንያም ወርቁም የቅጅ መብት ጥሰትና  ለኪነ ጥበብ ዘርፉ የሚያስፈልጉ ግብአቶች የተጋነነ ቀረጥ መጠየቁ ዘርፉን እንዳኮሰመነው ተናግረዋል። አክለውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡና ከውይይቱ ባሻገር ወደ ተግባር እንዲገባ፣ በዚያውም የተሻለ ስራ ለመስራት ርብርብ እንደሚያሻው ገልጸዋል።   በቀጣይም ተቋሙ የተነሱ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራም አቶ ይስማ ጽጌ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም